በጦርነቱ የተጎዳው ኢኮኖሚ እንዲያገግም መንግሥት ያስቀመጣቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት አስመዝግበዋል

71

አዲስ አበባ የካቲት 14/2014 /ኢዜአ/ በጦርነቱ የተጎዳው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም መንግሥት ያስቀመጣቸው የማሻሻያ እርምጃዎች አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከእነዚህም መካከል የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ መልሶ  እንዲያገግም የሚያስችሉ የማሻሻያ እርምጃዎች በማብራሪያቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ጊዜያት በሰው ሰራሽና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጨምሮ ጦርነት፣ በድርቅ፣ በጎርፍና በመሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ትልቅ ፈተና እንደገጠመው ተናግረዋል።

በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ ውጤቶች በችግሮች ውስጥ መልካም ተሞክሮ የተገኘበት እንደሆነ አንስተዋል።

ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የባንኮች ተቀማጭ ሃብትም ወደ 2 ትሪሊዮን ብር ከፍ ማለቱንና የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 50 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 46 በመቶ ማሳከት መቻሉን ገልጸዋል።

በወጪ ንግድ፣ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ቱሪዝምና ግብርና ሥራዎች ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልጸው ይህንንም የማጠናከር ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።  

የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚውን እየተፈታተነና የኑሮ ውድነት እንዲመጣ እያደረገ ያለ ትልቅ ተግዳሮት ሲሆን ለዚህም የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ዋነኛው ችግር መሆኑንም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት መዋቅር ሙስናን ለመከላከል ከታች እስከ ላይ አመራር አስፈላጊ ግምገማ በማድረግ የማስተካከል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዋጋ ግሽበት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለልም መንግሥት የሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ የማድረግ፣ የአገር ወስጥ ምርቶችን ማሳደግ፣ ድጎማ የመስጠትና የመሳሰሉት አማራጮች እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።   

የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ዳግም መልሶ ለማቋቋም እንደሚያስችል ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ የሚናገሩት።

በጦርነቱ ምክንያት የወደሙና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የተቀመጠው አቅጣጫም አዎንታዊ ውጤት እንደተመዘገበበት ተናግረዋል።  

የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎቹ በቀጣይ የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የኢኮኖሚ የማሻሻያ እርምጃ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ኢኮኖሚው ከሰላምና ከጠንካራ የሥራ ባህል ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑም መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመፈተሽ ከሌብነት በጸዳ አሰራር ሰፊ የሥራ ሁኔታ ማደራጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚው ከበለጸጉ አገራት ጋር የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከር ኢኮኖሚውን ማረጋጋትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚገባም ነው የገለጹት።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ትልቅ ስኬት መሆኑንና በቀጣይም የሃይል አቅርቦቱን በማሻሻል ኢኮኖሚው ላይ እመርታ ለማምጣት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም