በመዲናዋ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ኢትዮ-ጤና አውደ ርዕይና ጉባኤ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ

53

የካቲት 15/2014 /ኢዜአ/ በመዲናዋ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ኢትዮ-ጤና አውደ ርዕይና ጉባኤ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር አሰፋ ዓለም ገለጹ፡፡

6ኛው የኢትዮ-ጤና ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይና ጉባኤ ከየካቲት 26 እስከ የካቲት 28 በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር አሰፋ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ በጉባኤው በዋናነት በጤና እንክብካቤ፤ በህክምና መገልገያዎች እና በመድሃኒት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ምክክር እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በአውደ ርዕዩም ከዘጠኝ የተለያዩ አገራት የሚመጡና በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ በህክምና አገልግሎት ልህቀት፤ በታካሚ ደህንነት፣በጨረር እና ላቦራቶሪ ምርመራዎች እንዲሁም  በመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ አስመልክቶ ለባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

መድረኩ የእውቀት ሽግግርን በመፍጠርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ የህክምና እና የንግድ ባለሙያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ አምራቾች ፕሬዘዳንት ዳንኤል ዋክቶሌ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የመድሃኒት ማምረቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ መኖሩ ለአውደ ርዕዩ ተጨማሪ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለመድሃኒትና ለህክምና መገልገያ ግዥ በዓመት 50 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደምታደርግ ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 70 በመቶ የሚሆነውን በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ 12 መድሃኒት አምራቾች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው፤ የቂሊንጦ የመድሃኒት ማምረቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ ከጀመረ ወዲህ ተጨማሪ 29 ኩባንያዎች ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ሶስቱ በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አውስተዋል፡፡

6ኛው የኢትዮ-ጤና ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይና ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን፤ ከአሜሪካ፣ ባንግላዲሽ፣ ህንድ፣ ጆርዳን፣ሱዳን ፣ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚመጡ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡

ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች አውደ ርዕዩን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የመርሃ- ግብሩ አዘጋጆች ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም