የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግምባታ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

62

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የልማት ተግባራትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግምባታ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች በገንዘብና በአይነት እያደረጉት ላለው ድጋፍም ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ላይ ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራዊ የልማት እንቅስቃሴና በዴሞክራሲ ስርዓት ግምባታ እያከናወኑ ያለውን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከ3 ሺህ 600 በላይ የሲቪል ማህበራት የተቋቋሙበትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት ስላለባቸው ትርጉም ያለው ውጤታማ ተግባር ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ድርጅቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ አቅም እየገነቡና የማይናቅ አበርክቶ እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ በድርቅና በጦርነት የተነሳ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተደረገው ጥረት ውጤት ማምጣቱንም ጠቁመው፤ በተደረገው ድጋፍ በጦርነትና በድርቅ የተነሳ ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለማቃለል አስተዋጽኦ መደረጉን ተናግረዋል።

የማህበራት መበራከት ለማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ለዴሞክራሲ ስርአት መዳበር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፤ በስድት ወራት 390 አዲስ ማህበራትን ለመመዝገብ ታቅዶ 287 መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የባለስልጣኑን አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል ለማድረግ ድርጅቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

ከድርጅቱ ጋር የተደረገው ስምምነት አገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈና ዘመናዊ የሚያደርገው መሆኑን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም