የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አሸባሪው ህወሃት ለፈፀመው ግፍ እርምጃ እንዲወሰድበት ማድረግ አለባቸው

67

በአውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ዛሬ ባወጡት መግለጫ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አሸባሪው ህወሃት በአፋርና በአማራ ክልሎች ለፈፀማቸው ግፎች እርምጃ እንዲወሰድበት እንዲያደርጉ ጠየቁ።

ሁለቱ ህብረቶች የሰው ልጆች መብቶችን በሚጥሱ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የግንኙነታቸውን መርሆ ማክበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የህወሃት አመራሮች ኢትዮጵያን ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአገዛዝ ስር እንዳቆዩዋት በኋላም በህዝብ ታቃውሞ ከስልጣን ሲባረሩ ወደ ትግራይ በመሸሽ ህዝቡን መሸሸጊያ እንዳደረጉት መግለጫው አትቷል።

ይህ ቡድን የሰዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የሀሳብ ብዝሃነትን ጨምሮ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብቶችን ሲረግጥ እንደቆየም ጠቅሷል።

የሽብር ቡድኑ በቅርብ ጊዜ እንኳን መንግስት ያደረገውን የተኩስ አቁም በመጣስ  በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራ ማካሄዱን ያስታወሰው መግለጫው በወረራውም አሰቃቂ ግፎችን መፈፀማቸውን አብራርቷል።

በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ፣ በሴቶችና ህጻናት ላይ አስገድዶ መድፈር፣ በማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ብሏል።

የሽብር ቡድኑ ለእንስሳት እንኳን የሚራራ ልብ እንዳልነበረው በመጥቀስ እንስሳትን ከአካባቢው አርሶ አደር ከመዝረፉም ባለፈ በጥይት እየተኮሰ መግደሉን አብራርቷል።

የዳያስፖራ ማህበራቱ መግለጫ አሰቃቂ ግፎችን የፈፀመው አሸባሪው ህወሃት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት በመጥቀስም የሽብር ቡድኑ የፈፀማቸውን ማስረጃዎች እንደሚከተለው አቅርቧል፦

  በአማራና አፋር ክልሎች በሚኖሩ ሴቶችና ህጻናት ላይ በቡድን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ፆታዊ ጥቃት አድርሷል፤ በዚህም ሴቶችና ህጻናት ከፍተኛ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አንዳንዶችም በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ራሳቸውን እስከማጥፋት ደርሰዋል።

  በሁለቱ ክልሎች በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን መግደሉን በዓለም አቀፍ ገለልተኛ የምርምራ ተቋማት ተረጋግጧል።

  በአማራ ክልል ብቻ 40 ሆስፒታሎችን፣ 453 ጤና ጣቢያዎችን፣ 466 የግል ክሊኒኮችን በአፋር ክልል ደግሞ 57 የጤና ተቋማትን ከማውደሙ ባሻገር ህዝቡ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ የማድረግ ወንጀልም ፈጽሟል ነው ያለው መግለጫው።

 በሽብር ቡድኑ ጥቃት ከ7 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ከ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁና የመማር መብታቸው እንዲጣስ አድርጓል ብሏል።

  በትግራይ ክልል እያንዳንዱ ነዋሪ በአስገዳጅ ሁኔታ ልጆቹን ወደ ጦርነት እንዲልክ በማስገደድ ታዳጊዎችን ወደ ጦርነት መማገዱን እንዲሁም በከፈተው ጦርነት ምክንያት የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳያገኝ ማድረጉን ነው የጠቀሰው።

በአውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበራት አሸባሪው ቡድን ያደረሳቸውን አሰቃቂ ውድመቶች አውግዞ የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረቶች  የሽብር ቡድኑን ተጠያቂ እንደያደርጉት ጥሪ አቅርቧል።

አሸባሪ ቡድኑ ወደ አገዛዝ ከመጣበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለፈጸማቸው ግፎችም ገለልተኛ ምርመራ በማካሄድ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም