በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ክህሎት ያለው ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው

149

ጎባ ፤የካቲት 14/2014(ኢዜአ) በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ክህሎት ያለው ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ገለጸ፡፡

 "በአየር ንብረት ለውጥ፣አካባቢ ጥበቃና ስነ-ህዋ ሳይንስ ላይ የፊዚክስ ሚና" በሚል  መሪ ሀሳብ  ማህበሩና መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  ያዘጋጁት 16ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡  

የኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስገራ በዳሳ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ ማህበራቸው በህብረተሰቡ ዘንድ የፈጠራ ክህሎትን ለማሳደግ  ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ክህሎት ያለው ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር  በቅንጅት  እየሰራ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

ተቋማቱ  ምሁራንን በማሳተፍ የሚደረገው የምርምር ኮንፈረንስ ልምድና የፊዚክስ ዘርፍ  ግኝቶችን  በሰዉ ዘንድ ለማስረጽ  የጎላ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።

የመደ ወላቡ ዪኒቨርሲቲ የተሰጠውን የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተልዕኮዎችን በመወጣት ረገድ ተሰፋ ሰጭ ስራዎችን ቢያከናውንም በፊዝክስ ሳይንስና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል ናቸው።

ከሙያ ማህበሩ ጋር ሆነው በትኩረት መስራቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

ከምርምር ኮንፈረንሱ ያገኙትን  ምክረ ሀሳቦች ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ የሚገኘውን ምርምሮች ጥሩ ግብዓት እንደሚሆነውም ገልጸዋል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ተሾመ ሰንበታ፤ በአካባቢ ለውጥና በስነ-ህዋ ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ወቅታዊና የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቅርቡ ካስወነጨፋቸው የአካባቢ ምልከታ ሳተላይቶች አንዱ በዚህ ዘርፍ ላይ  ከተገኙ ውጤቶች  መካከል እንደሚጠቀሱ አንስተዋል።

ኮንፈረንሱ  አንጋፋና ነባር ምሁራን ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ልምድና እውቀት እንዳገኙበት የገለጹት ደግሞ ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተሳተፉት መምህር ኢብራህም ከድር ናቸው፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ኮንፈረንስ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ፣ አካባቢ ጥበቃና ስነ-ህዋ ሳይንስ ላይ ያተኮሩ 29 የምርምር ጥናቶች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ  የፊዚክስ ምሁራና አመራሮች በኮንፍረንሱ ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም