ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ተጨማሪ አምስት የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ከፈተ

102

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/2014(ኢዜአ) ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ተጨማሪ አምስት የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ከፈተ፡፡

ድርጅቱ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ በሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ከዚህ ቀደም 14 ጣቢያዎች የነበሩት ሲሆን፤ አሁን ላይ ተጨማሪ አምስት ጣቢያዎችን በመክፈት የጣቢያዎቹን ቁጥር ወደ 19 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ሳርካ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ጣቢያዎቹን መጨመር ያስፈለገው የአገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ ጣብያዎቹ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ነው ያነሱት፡፡

ተጨማሪ ጣብያዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ድርጅቱ ተጨማሪ ጣቢያዎቹን ስራ ባስጀመረበት መርሃ ግብር ላይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቻዎ ቺዩዋን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም