በህውሃት የሽብር ቡድን ጉዳት ለደረሰበት አምደ ወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

142

የካቲት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በህውሃት የሽብር ቡድን ጉዳት ለደረሰበት አምደ ወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ነው።

የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት፣የስርጭትና ስምሪት ዳይሬክተር አቶ እንዳለው አስማማው ለኢዜአ እንደገለፁት በሽብር ቡድኑ ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ በማቋቋም ስራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የተለያዩ የህክምና ግብአቶች ድጋፍ እየተደረጉ ነው።

ለአምደ ወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ድጋፉ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ፣ የእናቶች ማዋለጃ አልጋ እንዲሁም የቀዶ ጥገናና የቤተሙከራ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

አገልግሎቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ብርሃኑ አለሙ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በሽብር ቡድኑ በደረሰበት ውድመት ምክንያት የተሟላ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ያደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉን መለሶ ለማደራጀት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ግልሰቦችና ባለሃብቶች የሆስፒታሉን ችግር በመረዳት መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም