የኃያላን ሀገራት ጫና በመቋቋም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዳግም ያሳየ ነው

68

ባህር ዳር /ድሬደዋ/አዳማ /ሐረር / የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) ''አንዳንድ የኃያላን ሀገራት ያሳደሩብንን ጫና በመቋቋም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ  ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያዊያንን አሸናፊነት ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዳግም ያሳየ ነው'' ሲሉ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የባህር ዳር /ድሬደዋ/አዳማ /ሐረር / ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መላ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

ፕሮጀክቱ እውን እንዳይሆን ደግሞ የውስጥ ባንዳና ኃያላን ሀገራት ግንባር ፈጥረው ሀገሪቱን ለመበተን ሌት ተቀን ያደረጉት ጥረት በኢትዮጵያዊያን አንድነት ሊከሽፍ መቻሉን ተናግረዋል።

 "ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ኩራትና የህብረ ብሔራዊ እንድነት ምልክት ነው" ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንዲሆን ከተራ ግለሰብ ጀምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሻራ ያረፈበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የዛሬው ዕለት ግድቡ ከዳር እንዳይደርስ የኢትዮጵያን እድገት ከማይሹ ኃይሎች ጋር በማበር ከህዝብ የተሰበሰበውን ሀብት የመዘበሩት ቡድኖችና አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ያፈሩበት ነው ብለዋል።

አሁንም ወጣቶች፣ አዛውንት ሳንል የቀሩት የግድቡ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተጠናቀው ስራ እንዲጀምሩ ባለን አቅም ሁሉ መረባረብ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

ግድቡ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ የኢትዮጵያ ህዝብና የለውጡ አመራር የከፈለው መስዋትነት ከፍተኛ ቦታ ይይዛል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ግድቡ የአሁኑንና መጪውን ትውልድ ከልመና በማውጣት የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ እስከመጨረሻው ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማዕበላዊ ድጋፍና ፍቅር ታጅቦ፤ ህዝብና መንግሥት በእውነት ተቀናጅቶ፤በተናበበ ቁርጠኝነት ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የህዳሴ ግድብ ዛሬ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ መርጨቱ  አስደስቷል ።

"በህይወቴ እኔን የመሰሉ ወጣቶችና ሀገሬ በጠቅላላው  የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ሚበለፅግ ተሰምቶኛል፤የተደሰትኩበትም ታላቅ ቀን  ነው ያለው ግድቡ ከሚገነባበት ጉባ አካባቢ የመጣውና በድሬደዋ ላይ ሎተሪ በመሸጥ የሚተዳደረው ወጣት ታደለ ኤርሚያስ ነው።።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም