ኢትዮጵያ በግዙፉ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረች - አለም አቀፍና የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን

100

የካቲት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ በግዙፉ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረች”  ሲሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና በአፍሪካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ልዩ ልዩ የዘገባ ሽፋን ሰጥተዋል።

የቱርክ ዜና አገልግሎት አናዶሉ ቢሊዮን ዶላሮች የወጡበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መርቀውት የመጀመሪያው ምዕራፍ ኃይል መስጠት ጀመረ ሲል አስነብቧል።

በኢትዮጵያውያን የጋራ አቅም ቀስ በቀስ ግንባታው ተከናውኖ ኃይል ለማመንጨት በቅቷል ነው ያለው አናዶሉ በዘገባው።

ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ 60 በመቶ ኢትዮጵያውያንን ብርሃን ከመስጠት አልፎ ለጎረቤት ሀገራት በሽያጭ እንደሚቀርብ መነገሩን ዘግቧል።

አፍሪካን ኒውስ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨቱን በዳሰሰበት ዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕመድ የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያውን መርቀው መክፈታቸውን አንስቶ ‘አሁን ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል’ ማለታቸውን አስነብቧል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ለልማት የምትጠቀምበት በመሆኑ ግብጽና ሱዳን ስጋት ሊገባቸው አይገባል ይልቁንም እነሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ መናገራቸውንም አክሏል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 375 ሜጋ ዋት በማመንጨት የኃይል አገልግሎት መስጠት ጀመረ ሲል የዘገበው ናሽናል ኒውስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት የላትም ቀዳሚ አጀንዳዋ ብርሃን የማያገኙ እናቶችን ብርሃን ማሳየት ነው ማለታቸውን” አመልክቷል።

በተጨማሪም ዘገባው የግድቡ ኃይል ማመንጨት “የአዲስ ምዕራፍ ውልደት ነው” ሲሉ መግለጻቸውን አስነብቧል።

ሮይርትስ በበኩሉ “ኢትዮጵያ በግዙፉ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረች” በማለት ዘገባውን ጀምሮ  ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ግድቡ በተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚፈጥረው ጉዳት አለመኖሩን ይልቁንም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ማመልከታቸውን አስነብቧል።

የግብጹ አህራም ኦንላይንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረ ሲል ዘግቧል።

“የግድቡ ኃይል ማመንጨት ለአፍሪካውያንና ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መልካም ዜና ነው በጋራ ለመስራትም የሚያነሳሳ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመርሐግበሩ ላይ ያነሱትን ሀሳብ በዘገባው ዳስሷል።

“ኢትዮጵያ በግዙፉ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረች“ ሲል የዘገባ ሽፋን የሰጠው አልጀዚራ የግድቡን ታሪካዊ ዳራና አጀማመር አስታውሶ በግንባታው ሂደት ያጋጠሙ ሁኔታዎችን እና አሁን የደረሰበትን ደረጃ አስነብቧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም