በወላይታ ሶዶ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በግል ባለሀብት የተገነባ ሆስፒታል ለአገልግሎት በቃ

183

ሶዶ፣ የካቲት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወላይታ ሶዶ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በግል ባለሀብት የተገነባው 'እንያት ሆስፒታል' ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያደርግ መንግስት እንደሚያበረታታ የጤና ሚኒስቴር አረጋግጧል።

በእንያት ሆስፒታል ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የጤና ሚኒስቴርን ወክለው የተገኙት ዶክተር አባስ ሀሰን እንደገለጹት፤ የጤና ዘርፉን ሽፋን ለማሳደግ ከጤና ኬላ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ ነው።

ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለዜጎች ለማዳረስ የአመራሩን አቅም መገንባትና የሰለጠነ ባለሙያን በብዛት ማፍራት ትኩረት እንደሚሰጠውም ገልጸዋል።

የጤና መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ መሳሪያዎች የማሟላት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመው፤ ጥረቱ የግል ዘርፉንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የግሉ ዘርፍ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

በክልሉ 800 የሚጠጉ የግል የጤና ተቋማት እንዳሉ ጠቁመው፤ ተቋማቱ የሚያበረታታ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የእንያት ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አሸብር መዘነ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ ለ130 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ወደሌሎች አካባቢዎች የሚሄዱ ሕሙማንን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ገልፀው፤ ተቋሙ ለወላይታና አጎራባች ዞኖች አገልግሎት እንደሚሰጥ አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም