በጋምቤላ ክልል የታታ ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

73

ጋምቤላ፤ የካቲት 12/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የታታ ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የእንቦጭ አረም በሐይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የክልሉ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ንቅናቄ በሐይቁ መገኛ ጎግ ወረዳ የማስጀመሪያ ስነ- ስርዓት ተካሄዷል።

የታታ ሐይቅ የእንቦጭ አረም ባደረሰበት ጉዳት ከነበረበት 457 ሄክታር የውሃ ይዘት መጠን ወደ 251 ሄክታር ዝቅ እንዳለም ተመልክቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ጁል ናንጋል በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ሰፊ የገጸ ምድር የውሃ ሐብት ቢኖርም በአያያዝና በአጠቃቀም ረገድ በሚታዩ ችግሮች የታታ ሐይቅን ጨምሮ ከፍተኛ የውሃ ሀብት መመናመን እየታየ ነው።

የውሃ ሀብቱን አያያዝና አጠቃቀም በማሻሻል በዘላቂነት ለመጠቀም የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከቱሪስት መስብነቱ በተጨማሪ ከፍተኛ የዓሳ ምርት በሚገኝበት የታታ ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን  ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ዛሬ  በታታ ሐይቅ ላይ የተጀመረው የእንቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ በማስቀጠል ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ ፤ታታ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪና ለዓሳ ሃብት ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ  ያለው ሐይቅ ነው ብለዋል።

ሆኖም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንቦጭ አረም ባደረሰበት ጉዳት የሐይቁ ስፋት ከመቀነሱም በተጨማሪ የዓሳ ምርት መጠኑም እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሐይቁ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል የሁሉን ባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ እንደሚያሻ አስታውቀዋል።

ሐይቁ ቀደም ሲል 457 ሄክታር ስፋት እንደነበረው የገለጹት ደግሞ የክልሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንዳር ኡማን ኡጋላ ናቸው።

የእንቦጭ አረምና አካባቢ መራቆት ምክንያት አሁን ላይ የሐይቁ ስፋት 251 ሄክታር ብቻ መቅረቱን አስረድተዋል።

በእንቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ ማስጀመሪያ በመረሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም