ወጣቱ ከጀግኖች አባቶች ሕብረትን ተምሮ ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆምን ሊያጠናክር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ከጀግኖች አባቶች ሕብረትን ተምሮ ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆምን ሊያጠናክር ይገባል
ባህር ዳር፣ የካቲት 12/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ ጠላቶች ሲነሱ ጀግኖች አባቶች ከነበሯቸው ሕብረት ተምሮ ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆምን ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር እና የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ዛሬ እየተከበረ ያለውን የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ በዓል አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ወጣት ዘላለም ታከለ እንዳለው በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የተነሱ ጠላቶች በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ አድርሰዋል።
የጣልያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማስተዳደር ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ በአድዋ የድል ታሪክ መክሸፉን አስታውሷል።
በእዚህ የተበሳጨውና የተቆጨው ወራሪው ኃይል ለዘመናት ሲዘጋጅ ቆይቶ ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው ወረራ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን በጅምላ ፈጅቷል።
ለእዚህም በ1929 ዓ.ም በዛሬዋ ቀን በጨካኙ ግራዚያኒ ይመራ የነበረው የጣልያን ወራሪ ጦር በአዲስ አበባ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን አስታውሷል።
ግድያውና ጭፍጨፋው ብሔርንና ማንነትን መሰረት አድርጎ ሳይሆን መላው ኢትጵያዊያንን ጠላት አድርጎ በመውሰድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የካቲት 12 በኢትዮጵያ በመጥፎ ትውስታቸው ከሚጠቀሱ ቀናቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሶ፣ በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በግፍ የተረሸኑት በኢትዮጵያዊነታቸው እንደሆነ ተናግሯል።
ቀኑ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ሲሉ ዘር፣ ሃይማኖትና ፆታ ሳይገድባቸው ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያዘጋጁበት ቀን እንደነበረም ወጣት ዘላለም ገልጿል።
ዛሬ ላይ ወጣቱ በጽንፈኛ እና ማህበረሰብ አንቂ ነን በሚሉ አካላት ለሚያሰራጩት ከፋፋይ ሀሳብ ጆሮ ሳይሰጥ የአባቶቹን የኋላ ታሪክ በማየት ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆምን ማጠናከር እንዳለበት ገልጿል።
"ዩቲዩብን መተዳደሪያቸው ባደረጉና ልዩነትን በሚሰብኩ አካላት ሳንታለል እንደ ጀግኖች አባቶች ሕብረትን በማጠናከር የአገራችንን ሉዓላዊነት ጠብቀን ማቆየት ይኖርብናል ብሏል።
"ወጣቱ ስለሀገር ፍቅርና አንድነት እንዳያስብ ለ27 ዓመታት ቢሰራበትም ሀገሩን ከጠላት ለመታደግ ዛሬም እንዳባቶቹ በጋራ ቁሟል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው ናቸው።
በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ መከራና እንግልት ማድረሳቸውንም ገልጿል።
አቶ ዳኝነት እንዳሉት የጣሊያን ፋሺስት ወራሪ የካቲት 12 በአዲስ አበባ ከሕጻን እስከ አዛውንት በርካታ ንጹሀንን ሲጨፈጭፍ ማንነትን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን መሰረት በማድረግ ነው።
ጀግኖች አባቶች አንድነታቸውን በማጠናከራቸው ለወራሪው ፋሺስት ሳይበገሩ ኢትዮጵያን አስከብረው ቆይተዋል።
የዛሬ ወጣትም የቀደምት አባቶቹን የአንድነት ታሪክ መለስ ብሎ በማየት ለአንድነቱና ለአገሩ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት መክረዋል።
የዛሬ 85 ዓመት ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን በሃይል ተቆጣጥሮ የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ በሚጥርበት ወቅት ከ30 ሺህ በላይ ንጹሃን ወገኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፉ በታሪክ የሚታወስ ነው።