በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ የተገነባ የካንሰር ህክምና ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

66

ጅማ፣ የካቲት 12/2014 /ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የካንሰር ህክምና ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

ማዕከሉ በተመረቀበት ሥነ-ሥርዓት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በጤናው ዘርፍ  ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከምና ለመከላከል እየሰራ ነው።

የካንሰር ህክምና ለበርካታ ዓመታት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ  ይሰጥ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ህመምተኛው እስከ ስድስት ወራት ተራ መጠበቅ እንደሚገደድ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩን ለማቃለል እየተደረገ ካለው ጥረት መካከል የጅማ የካንሰር ህክምና ማዕከል ስራ ማስጀመር አንዱ ነው ብለዋል።

በሀገራችን በ17 ሆስፒታሎች የ"ኬሞ ቴራፒ" እና የጨረር የካንሰር ህክምና ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ሚኒስትሯ።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በካንሰር ከተያዙ ከ70ሺህ በላይ ሰዎች መካከል የህክምና አገልግሎት የሚያገኙት ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸዋል።

በተለይም የካንሰር በሽታ ሴቶችን የሚያጠቃ በመሆኑ ታማሚዎች ህክምናውን ቀድመው እንዲጀምሩና እንዲከላከሉ በየደረጃው ግንዛቤ የመስጠት ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሀይለማርያምና ሮማን የካንሰር ማዕከል መስራች የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንዳሉት፤ የጅማውን ጨምሮ በሀገሪቱ  የካንሰር ማዕከላት 17 ደርሰዋል።

የካንሰርን ቅድመ መከላከል ስራ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ሮማን፤ የማህጸን በር ጫፍና  የጡት ካንሰርን ለመከላከል እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የካንሰር የህክምና ማዕከሉ ስራ እንዲጀምር በጉጉት የሚጠብቁ  የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን  የተናገሩት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  ውስጥ በተገነባው የህክምና ማዕከል ህብረተሰቡን በአግባቡ ለማገልገል ተዘጋጅተናል ብለዋል።

 ለማዕከሉ ግንባታ  ከ350ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም