በመንዲ ከተማ በ19 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ መሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው

59

ግምቢ የካቲት-12/2014/ (ኢዜአ)---በምዕራብ ወለጋ ዞን የመንዲ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በ19 ሚሊዮን ብር የተለያዩ መሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍቃደ ታሲሳ እንደገለፁት የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ የሆነውን መሰረተ ልማት ለመመለስ እየተሰራ ነው።

በከተማዋ እየተከናወኑ ካሉ የልማት ፕሮጀክቶች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ፣የኤሌክትሪክ መብራት መስመር፣ ወደ አራት ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ እና የኮብል ስቶን ንጣፍ መንገድና በቡኡራ ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት የ14 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ይገኙበታል።

ከንቲባው እንዳሉት በከተማዋ በዚህ ዓመት እየተካሄዱ ያሉት  21 ያህል የልማት ፕሮጀክቶች ከ1 ሺህ 320 ለሚበልጡ  ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል።

የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የከተማው ነዋሪዎች ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ፍቃደ አሳስበዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከሶስት ዓመት ወዲህ በከተማው የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ እያዩ ነው።

ከመንዲ ከተማ ነዋሪዎች አቶ ጫንያለው ፍቃዱ እንዳሉት እየተገነቡ ያሉት የመሰረተ ልማት ስራዎች የከተማዋን ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ናቸው ብለዋል።

ክረምት በጭቃ በጋ በአቧራ ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው አሁን የውስጥ ለውስጥ የኮብልስቶን ንጣፍ  እየተሰራ በመሆኑ ችግሩ መፍትሄ እንደሚያገኝ እምነታቸው ገልጸዋል።

አቶ ካሳ አረጋ በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት የልማት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ መሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ለአገልግሎት ሲበቁ እያዩ በመሆኑ ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡

ሌላው የመንዲ ከተማ ነዋሪ አቶ ታደለ ሙለታ እንደተናገሩት በከተማው የህዝቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ሰሚ አጥቶ የቆየው የህዝቡ ጥያቄ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ምላሽ እያገኘ መምጣቱ መልካም ጅምር መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ታደለ አክለውም በከተማዋ  እየተሰሩ ያሉት መሰረተ ልማቶችን ከአስተዳደሩ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም