በሌላ ሰው የሒሳብ ቁጥር ከባንክ ገንዘብ አጭበርብሮ እንደወሰደ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በሌላ ሰው የሒሳብ ቁጥር ከባንክ ገንዘብ አጭበርብሮ እንደወሰደ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ
ጭሮ፤ የካቲት 12/2014 (ኢዜአ) ከአቢሲንያ ባንክ ሁለት ቅርንጫፎች በሌላ ሰው የሂሳብ ቁጥር 30 ሺህ ብር አጭበርብሮ እንደወሰደ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የጭሮ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ካሳሁን ባይሳ እንደገለጹት፤ ግለሰቡ ገንዘቡን አጨብርብሮ ከወሰደባቸው መካከል 15 ሺህ ብር ከባንኩ ጭሮ ቅርንጫፍ ነው።
ግለሰቡ በዚህ ቅርንጫፍ የካቲት 10/2014 ዓ.ም የገንዘብ ማውጫ ማዘዣ ላይ የራሱ አስመስሎ ገዛኸኝ ከተማ የሚለውን ስም በመጻፍ ለገንዘብ ከፋዩ በመስጠት ነው ያጨበረበረው ፡፡
በዚህም ገንዘቡን ከከፋዩ ከወሰደ በኋላ በፍጥነት ከእይታ ለመሰወር ቢሞክርም መረጃው የደረሳቸው የባንኩ ጥበቃ ሰራተኛ ከማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ፓትሮልና ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር መዋሉን ዋና ሳጂን ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቡ ሳሳን ባንተ ነኝ ብሎ ራሱን ቢገልጽም ትክክለኛ ማንነቱና አድራሻው እየተጣራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰሞኑን በሂርና ከተማ ከሚገኘው የአቢሲንያ ባንክ ጡሎ ቅርንጫፍ 15 ሺህ ብር ያወጣ መሆኑም ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
በተደረገው ፍተሻም ሰባት የተለያዩ ሰዎች መታወቂያዎች ይዞ መገኘቱም ታውቋል፡፡
ለተጨማሪ ምርመራ የግለሰቡን ጉዳይ ለጡሎ ወረዳ ፖሊስ መላኩን ዋና ሳጅን ካሳሁን ባይሳ ገልጸዋል፡፡