በምዕራብ ሀረርጌ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ

90

ጭሮ፤የካቲት10/2014(ኢዜአ)--- በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ሁለት ወረዳዎች ከ2 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ አደጋ ስጋት አመራርና ልማት ተነሺዎች ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አልፊያ አልዪ እንዳሉት በዞኑ ሀዊ ጉዲና እና ቡርቃ ዲምቱ ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የተደረገው ድጋፍ ከዞኑና ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች የተሰበሰበ ነው።

ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች 1ሺህ 200 ኩንታል የተሰበሰበ ሲሆን፤ ቀሪው 1ሺህ ኩንታል ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተደረገ ድጋፍ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከዚህም ባሻገር በሁለቱ ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ያጋጠመውን የውሃ ችግር ለማቃለል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ 11 ቦቴ ውሃ መቅረቡን ገልጸዋል።

ሀዊ ጉዲና እና ቡርቃ ዲምቱ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ቆላማ አካባቢዎች በመሆናቸው ለድርቅ  ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ቀጣይ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጉምቢ ቦርደዴ፣ ሚኤሶና ኦዳቡልቱም ወረዳዎች ከፊል ቆላማ የአየር ንብረት ያላቸው በመሆኑ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ከበደ እንዳሉት ከየቦታው ተሰብስቦ በሚሰጥ ድጋፍ ብቻ ችግሩን ማቃለል እንደማይቻል ጠቁመው፤ የመስኖን ልማትን በማጠናከር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል።

በረሃማነት በሚያጠቃቸው የዞኑ አካባቢዎች አነስተኛ ግድቦችን በመገንባት የውሃ እጥረትን ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ አርሶ አደሮች የሚታየውን የአመራረት ችግር በማቃለል ድርቅን መከላከል አንዱ ስራ መሆኑንም አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ በሰባት ወር በሚደርሰው ማሽላ ላይ ከማተኮር ይልቅ በሦስት እና በአራት ወር በሚደርሱ እንደ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሾ የመሳሰሉ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አነስተኛ ግድቦችን በማስፋፋት በዞኑ ከሁለት ዓመት በኋላ ለድርቅ ተጋላጭነትን በ80 በመቶ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የሀዊ ጉዲና ወረዳ ነዋሪ አቶ አህመድ መሃመድ አካባቢያቸው የዝናብ እጥረት ያለበት በመሆኑ በበጋ ወቅት ውሃ ስለሚጠፋ ለድርቅ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ አህመድ በችግራቸው ጊዜ አለሁ ላላቸውና ካለው ቀንሶ ላካፈላቸው ህዝብም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቀጣይ አካባቢያቸው በድርቅ እንዳይጠቃ በመስራት በረሃማነትን ለማጥፋት ዛፎችን ለመትከል ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የቡርቃ ዲምቱ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፋይዛ ኢብራሂም ልጆቻቸውና ቤተሰባቸው እንዳይራቡ የምግብ እህልና የውሃ ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ አመስግነዋል።

ዳግም የውሃ እጥረትና በረሃማነት እንዳያጠቃቸው ዛፎችን በመትከልና በመስኖ ልማት በመሰማራት ለመለወጥ መነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም