በአፋር ክልል የጥጥ እርሻ ልማትን በማስፋት ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

144

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/ በአፋር ክልል የጥጥ እርሻ ልማትን በማስፋት ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስትቲዩት ገለጸ።

በኢትዮጵያ ካሉ ጥጥ አብቃይ አካባቢዎች የአፋር ክልል ዋነኛው ሲሆን በአካባቢው የሚመረተው የጥጥ ዝርያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ መሆኑ ይነገራል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጥጥ በስፋት ማምረት ከሚችሉ አገራት መካከል ብትሆንም እምቅ ሃብቷን እየተጠቀመችበት አለመሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሰለ መኩሪያ፤ በአፋር ክልል በተለይ የጥጥ እርሻ ልማትን በማስፋት ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የማምረት ስራው ተዳክሞ የነበረውን የጥጥ ልማት ስራ እንደገና ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል የሚመረተው ጥጥ ደረጃውን የጠበቀና ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ ልማቱን በስፋት የማካሄድ ስራ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የጥጥ አብቃይ መሬት ለስንዴ ምርትም ምቹ በመሆኑ የጥጥ እርሻውን ተከትሎ የስንዴ ምርትንም ማልማት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በአካባቢው የመስኖ መሰረተ ልማት፣ በመሬት ፖሊሲና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮች እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግና የስራ እድል እንዲፈጠርበት የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በክልሉ የጥጥ ምርት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ከመሆኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ገበያም ጭምር ተፈላጊ በመሆኑ አልሚዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀርቧል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 70 በመቶ የሚሆነውን የጥጥ ገበያ የሚሸፍኑት ህንድ፣ አሜሪካና ቻይና መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም