በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የፊታችን ሰኞ ይጀመራል

63

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤቱ ስር ያሉ ተጠሪ ተቋማት የ2014 በጀት ዓመት አጋማሽ የስራ አፈፃጸም ተገምግሟል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በተለይም በጽዳት አስተዳደር በኩል የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ሁነቶችን ታሳቢ በማድረግ የተከናወኑ የጽዳት ስራዎች ለታየው ጥሩ አፈጻጸም አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው የታየው በጎ ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የተደረገው ጥረትም አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥና በእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት አመራር በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ግን በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በከተማዋ ተቋርጦ የቆየው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የፊታችን ሰኞ ዳግም አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ በላቸው፤ በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በኩል መልካም ክንውኖች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከገጸ ምድር ከ37  ነጥብ 2  ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ፤ ከነባር ከርሰ ምድር ደግሞ ከ68 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ በማምረት ማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት።

በወሳኝ ኩነትም በስድስት ወራት ከ613 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዝግቦ የመያዝ ስራ መከናወኑን ጠቁመው በቀጣይ ያለውን አፈጸጻም ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላትና ጠንካራ ጎኖችን ለማዳበር በሚያስችል መልኩ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም