ኢትዮጵያና ጃፓን የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

55
አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 ኢትዮጵያና ጃፓን ትብብራቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ማበረታቻ ስምምነት ለመፈራረም ተስማሙ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኬንታሮ ሶኑራ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ነው የመከሩት። በውይይቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንዲቻል የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች መካከል በየጊዜው በሚካሄደው መደበኛ የምክክር መድረክ ላይ ጉዳዩን ዋና አጀንዳ አድርጎ በመያዝ በአጭር ጊዜ የኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ማስፋፊያና ከለላ የጋራ ስምምነት ለመፈራረም ተስማምተዋል። በተጨማሪም የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የአደረጃጀት ፍትሃዊነትን የማሻሻል አጀንዳን በማራመድ፣ ድንበር ተሻጋሪ የጋራ ሃብትን ለጋራ ልማት መጠቀምን በማረጋገጥ፣ የባህር ላይ ውንብድናን ጨምሮ በሌሎች አካባቢያዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን በሚመለከትም በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል። ፕሮፌሰር አፈወርቅ ኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በላይ ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና በየጊዜው ተገቢ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያዎች በማድረግ ውስጣዊ ጥንካሬን እያሳደገች መምጣቷን አስረድተዋል። የሁለቱ አገራት ግንኙነትም ከዕድገቱ ጋር በሚመጋገብ ሁኔታ እያደገ መሆኑንና ይበልጥ እንዲጠናከርም እየተሰራ ነው ብለዋል። የጃፓን መንግስት ኢትዮጵያ ስደተኞችን ከመቀበል ጀምሮ በተናጠልም ሆነ በኢጋድ በኩል የባህር ላይ ውንብድና ጨምሮ ለጃፓንና ለሌሎች ያደጉ አገራት ጭምር ስጋት ለሆኑ ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት እየተጫወተች ያለውን ሚና ተገንዝቦ የሚያደርገውን ድጋፍ እያሰፋ መምጣቱን አድንቀው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኬንታሮ ሶኑራ አገራቸው በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችንና ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የሰላም ሂደት እንደምትደግፍ ገልጸዋል። መንግስታቸው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚውል ተጨማሪ እገዛ ለማድረግና የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደትን ጨምሮ በሌሎች የጋራ አካባቢያዊና አለምዓቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ አስረድተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች በደቡብ ኮርያና በአሜሪካ መካከል ስለተጀመረው የሰላም ሂደትም ተወያይተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም