ረቂቅ ህጉ ለኮንግረንሱ እንዳይቀርብ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተናጠልና በቡድን እየተሟገቱ ነው

56

የካቲት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰሞኑን በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ህግ ለኮንግረንሱ ቀርቦ እንዳይጸድቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተናጠልና በቡድን እየተሟገቱ መሆኑን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብረኃይል አስተባባሪዎች ተናገሩ።

በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉደይ ኮሚቴ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን የሚፈጥር ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ህግ ማሳለፉ ይታወሳል።

ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫናዎችን የሚፈጥሩ ድንጋጌዎች ማካተቱን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብረኃይል አስተባባሪዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መልዐከህይወት እንዳሉት ረቂቅ ህጉ ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ብድርና እርዳታዎች እንዲቆሙ ይጠይቃል።

በተለይም በውጭ ያለው ማህበረሰብ የሚልካቸው እርዳታዎች እንዲቆሙና ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ እገዛ ለኢትዮጵያ እንዳያደርጉ ከመጠየቁም ባሻገር በዴሞክራትና በሪፐብሊካን ተወካዮች መደገፉ የከፋ ያደርገዋል ብለዋል።

ረቂቅ ህጉ የአሜሪካንና የህዝቧን ፍላጎት የማያንጸባርቅ መሆኑን ያነሱት ሌላኛው የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪ አቶ መስፍን አስፋው ከህወሃት ጋር አጋርነት ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የራሳቸውን ጥቅም በጫና ለማስከበር የሚሞክሩ ኃይሎች ‘ኤች አር 6600’ን ማዘጋጀታቸውን በመጥቀስ በመከባበር እንጂ በጫና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈልጉትን ማስፈፀም እንደማይቻል ሊነገራቸው ይገባል ነው ያሉት።

የግብረ-ኃይሉ ሌላኛው አባል አቶ ፋሲል አጥሌ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለመጉዳት በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ለአግባቢዎችና ለአሜሪካ ፖለቲከኞች እየከፈለ እንደነበርና አሁንም እንደሚከፍል ተናግረዋል።

May be an image of 1 person and sitting

የህወሃትን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት የሚሰሩ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ አሁንም ‘ኤች አር 6600’ እንዲጸድቅ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ዳያስፖራው ረቂቅ ህጉ እንዳይፀድቅ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ይሰራል ነው ያሉት።

አቶ መስፍን አስፋው ረቂቅ ህጉ የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት ፈፅሞ የሚጎዳ በመሆኑ በኮንግረንስ የመሰብሰቢየ አዳራሽ መቅረብ እንደሌለበትም ተናግረዋል።

May be an image of 1 person and wrist watch

ረቂቅ ህጉን ኢትዮጵያውያን እንደ ቅኝ ግዛት ሙከራ እንደሚቆጥሩት ጠቅሰው ለኮንግረንሱ ውይይትና ውሳኔ እንዳይቀርብ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተናጠልና በቡድን እየተሟገቱ መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ ጣሰውም ረቂቅ ህጉ ወደ ኮንግረንሱ እንዳይቀርብ በርካታ የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪክ፣ የዲፕሎማሲ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በትጋት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በ”በቃ” ዘመቻ የታየው አንድነት በአሁኑ የፀረ ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ህግ የተቃውሞ ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም