ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በመጪው ሰኞ በባህርዳር ከተማ አቀባበል ይደረግለታል

49
ባህር ዳር ነሀሴ 26/2010 በመጪው ሰኞ ባህርዳር ከተማ ለሚገባው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ። “አንድ ሆነን ስለኢትዮጵያችን በፍቅር እንጓዛለን፤ ከሚሊዮን ወርቅ ለአንዷ ሰንደቅ የሚወድቅ” በሚል መሪ ሃሳብ አቀባበል እንደሚደረግለት አስተባባሪ ኮሚቴው ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የአቢይ ኮሚቴው አስተባባሪና የባህርዳር ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ እንደገለጹት አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በመጭው ሰኞ ጥዋት ባህርዳር ይገባል። ከጥዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮም በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም በመንግስት አካላት፣ በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ ህዝብ አቀባበል ይደረግለታል፡፡ አርቲስትና አክቲቢስት ታማኝ በየነ ነሐሴ 29 ቀን 2010 ከከተማዋ ነዋሪ ተወካዩችና አመራሮች ጋር  በክልል ምክር ቤት ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል። አቀባበሉንም የሚያስተባብሩ 2ሺህ የሚደርሱ የከተማዋ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። የፀጥታ አስከባሪ አካላትም አቀባበሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም