በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተፋሰሶችን አርሶ አደሮች መልሰው እያለሙ ነው

79

ሰቆጣ፤ የካቲት 11/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የወደሙ ተፋሰሶችን በእልህና በቁጭት መልሰው እያለሙ መሆኑን በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የደሃና ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በወረዳው  የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ተጀምሯል።

በወረዳው የጋኪው ቀበሌ  አርሶ አደር ጸሐይነው ሙጨየ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው ያለሟቸው ተፋሰሶች በማገገማቸው  ለእንስሳት እርባታ ጠቀሜታ ሰጥቷቸዋል።

ሆኖም አሸባሪው የህወሓት ቡድን  በወረዳው  ወረራ በፈፀመበት ወቅት ቀደም ሲል በተፋሰሶች ውስጥ የተሰሩ እርከኖችን ከማፍረሱም ባለፈ የለማ ደን ማውደሙን ገልጸዋል።

''አሁን ላይ አካባቢያችን ከሽብር ቡድኑ ነፃ በመሆኑ ወደ ልማቱ አተኩረናል'' ብለዋል።

በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት  ስራም በሽብር ቡድኑ የተጎዳውን ተፋሰስ መልሰው በመገንባት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚያግዙ የልማት ስራዎችን በእልህና ቁጭት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ምህረት ደሴ በበኩላቸው፤ በቀበሌው ካሁን ቀደም ባከናወኗቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች  የለማው ተፋሰስ ምንጮች እንዲፈልቁ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመበት ወቅት ጉዳት ያደረሰባቸውን ተፋሰሶች መልሶ በመገንባትም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያስታወቁት።

"የተፈጥሮ ሀብት ስራ ለአርሶ አደሩ ህይወት መቀየር ዓይነተኛ አማራጭ ነው" ያሉት አርሶ አደሯ፤  የሚሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች በአግባቡ ተከልለው እንዲለሙ የበኩላችውን  እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የድሃና ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን መንግስቴ፤ በወረዳው ባለፉት ዓመታት በ151 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራ መከናወኑን አስታውሰዋል።

ካሁን ቀደም ከለሙ ተፋሰሶች ውስጥም 132 ያህሉ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመው፤ የወረዳው አርሶ አደሮችም ጉዳት የደረሰባቸውን ተፋሰሶች በእልህና በቁጭት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ ስድስት ወረዳዎች በ310 አዲስና ነባር ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አስፋው ታፈረ ናቸው።

በሽብር ቡድኑ የወደሙ የተፋሰስ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት አርሶ አደሩ በቁጭት የልማት ስራውን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለ15  ቀናት በሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ  በዞኑ ከ87 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚሳተፍ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም