አገራዊ ምክክሩን ህዝቡ በነፃነት፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲጠቀምበት ለማስቻል የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩን ህዝቡ በነፃነት፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲጠቀምበት ለማስቻል የድርሻችንን እንወጣለን
አዲስ አበባ የካቲት 11/2014(ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩን ህዝቡ በነፃነት፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲጠቀምበት ለማስቻል የድርሻችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ የአዲሰ አበባ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
የምክር ቤት አባላት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባል ኡስታዝ ሰይድ አሊ፤ የምክክር ኮሚሽኑ ለዘመናት ሲጓተቱ የመጡ ችግሮች እንዳይቀጥሉ በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
በምክክሩ እንደ አገር ሁለንተናዊ ችግሮች ተዳሰውበት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ መሰረቷ ጠንካራ የሆነች አገር ለመገንባት ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ኢቲሳ ደሜ፤ የምክክር ኮሚሽኑን አስፈላጊነት በማንሳት ለረዥም ጊዜ የቆዩ ልዩነቶችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በምክክሩ ልዩነቶችን በማስተናገድ አንድ በሚያደርጉ የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ለምክክሩ ውጤታማነት ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ኖሮት እንዲሳተፍ በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው የምክር ቤት አባላት የተናገሩት።
በሚደረጉ ውይይቶች ህዝብ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሃሳቡን እንዲገልጽም ከወዲሁ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም በልዩነቶች ዙሪያ ተቀራርቦ በመነጋገር ልዩነቶችን በማጥበብ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር በማሰብ አገራዊ የምክክር የኮሚሽን መቋቋሙ ይታወቃል።