የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ጥቅም ላይ ልታውል ይገባል

105

የካቲት 11/2014/ኢዜአ/ የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ጥቅም ላይ ልታውል እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ፤ የ13 ወራት ጸጋና የተስማሚ አየር ንብረት ባለቤት ብትሆንም ድርቅ ተመላልሶ ጉዳት ከሚያደርስባቸው አገሮች መካከል ትጠቀሳለች።

በመሆኑም ድርቅ በየጊዜው የሚያስከትለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አለባት ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብደላ ከማል፤ ኢትዮጵያ በተለይም በገጸ ምድር የውሃ ሃብት የታደለች አገር መሆኗን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከገፀ ምድር የተፋሰስ ወንዞች በአመት 124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያላት ሲሆን ከ36 እስከ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት እንዳላትም ይገመታል።

ከገፀ ምድር የውሃ ሃብቷ 83 በመቶ የሚገኘው ከተከዜ፣ ባሮ፣ አባይና ጊቤ ኦሞ ወንዞች ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወንዞቿን እምብዛም ለልማት አለማዋሏን ዶክተር አብደላ ይናገራሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም የውሃ ሃብቷን በአግባቡ ጥቅም ላይ ልታውል ይገባል ነው ያሉት።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዕፀዋት ሳይንስ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ችግኜ አዳሙ፤ በኢትዮጵያ በየአሰር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ላይ በየሶስት ዓመቱ እየተከሰተ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም የድርቅ አደጋዎችን በዘላቂነት መቋቋም የሚቻለው በኢትዮጵያ ያሉ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሃብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ “በቆላማ አካባቢዎች በረጅም ጊዜ እቅድ እስከ ስምንት ወራት ውሃ መያዝ የሚችል ግድብ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል የግብርና ምርምር ተቋም ተመራማሪ ሙሉጌታ ማርቆስ፤ የድርቅን መከሰት መከላከል ስለማይቻል ተቋቁሞ ለማለፍ ግን የመፍትሄ አማራጮችን መከተል ይገባል ይላሉ።

በተለይም ያደጉ አገራት የኢንዱስትሪ ተጠቃሚነታቸው በእጅጉ በማደጉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አዳጊ አገራት ላይ የጎላ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም