የኢሉ አባቦር ነዋሪዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብ እህልና የእንሳስት መኖ ድጋፍ አደረጉ

65

አዳማ ኢዜአ የካቲት 10/2014...የኢሉ አባቦር ዞን ነዋሪዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብ እህልና የእንሳስት መኖ ድጋፍ አደረጉ ።

የኢሉ አባቦር ዞን የአደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሽዎች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ታሪኩ ሳምቢ ድጋፉን ለምስራቅ ሸዋ ዞን የአደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ የእህል ድጋፍ ማድረጋቸውን ተወካዩ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የእንስሳት ሀብቱን ለመታደግ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውን የእንስሳት መኖ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዞኑ ማህበረሰብ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ታሪኩ አረጋግጠዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን የአደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ተማም ሁሴን እንዳሉት ፈንታሌን ጨምሮ በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች በድርቅ የተጎዱ እንስሳትን ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ ነው።

የዞኑ ህብረተሰብ ከምግብ እህል ጀምሮ የእንስሳት መኖ ጭምር እርስ በርስ እንዲረዳዳ የተቀናጀ ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ግመሎችና ፍየሎችን ጨምሮ ሌሎች እንስሳትን በዞኑ ውሃና መኖ በቀላሉ ወደ ሚያገኙበት አካባቢዎች በማንቀሳቀስ ከከፋ ጉዳት ለመታደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ፍሬዘር አበራ በበኩላቸው በወረዳው የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመቋቋም ከዞኑ አስተዳደር ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ ነው።

የኢሉ አባቦር ማህበረሰብና ነዋሪዎች ያደረጉት ድጋፍ የኦሮሞን የመረዳዳት ባህልን በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም አመስግነዋል።

ከፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ሃጂ ሐዋስ አቦምሳ በበኩላቸው የኢሉ አባቦር ነዋሪዎች ያደረጉላቸው ድጋፍ እየተፈታተናቸው ያለውን ድርቅ ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ገልጸው አመስግነዋል።

ሌሎችም ድርቅ ያልደረሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ነዋሪዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ከቤት እንስሳት ቀጥሎ እየተጎዱ ያሉት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸው ወይዘሮ በሪቴ ፈንታሌ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ እንደ ኢሉ አባቦር ነዋሪዎች ሁሉ ሊያግዟቸውና ከጎናቸው እንዲቆሞ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም