የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት

77

ሰቆጣ የካቲት 10/2014(ኢዜአ) -የእንጅባራ መምህራን ኮሌጅ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰበት የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የእንጅባራ መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ሽቱ አየነ ዛሬ ድጋፉን ሲያስረክቡ፤ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

በዚህም የተማረ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ የትምህርት ተቋማት ጭምር በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

"ካለን እናካፍል" በሚል በቡድኑ ጉዳት የደረሰበትን የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ መልሶ ለማቋቋም የ340 ሺህ ብር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አስረክበዋል።


ድጋፉም 200 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ፤  140 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የወረቀት፣ የኮምፒተር እና የፕሪንተር ቀለሞች ናቸው።

በቀጣይም ሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ ወደቀደመ የመማር ማስተማር ሥራው በተሟላ ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ ኮሌጁ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አቶ ሽቱ አረጋግጠዋል።

የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ጌታሁን አዳነ በበኩላቸው፤ በወራሪው ህወሓት ምክንያት ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮሌጁ ንብረት ለዝርፊያና ውድመት መዳረጉን ገልጸዋል።


በዚህም ለመምህራን ስልጠና ግልጋሎት ሲሰጡ በነበሩ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጻህፍት፣ የኮፒውተር ማዕከል ውስጥ የነበሩ የማሰልጠኛ ግብአቶች መዘረፋቸውን አመላክተዋል።

በእንጅባራ መምህራን ኮሌጅ የተደረገው ድጋፍ የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመርና አስተዳደራዊ ሂደትን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን በመግለጽ  ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ኮሌጁ ወደ ቀደመ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲመለስ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም