የኢትዮጵያን ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የምርት ጥራትን ማስጠበቅ ይገባል

85

የካቲት 10/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የምርት ጥራትን ማስጠበቅ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በብሔራዊ የጥራት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

ረቂቅ ሰነዱ የምርት ጥራትን ጽንሰ ሐሳብ፣ ጥራት ላይ መሥራት ያለው አዎንታዊ ፋይዳ፣ ክፍተቶቹንና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድርሻን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፤ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ለምርት ጥራት ማስጠበቅ የሁሉም የጋራ ጥረት ያስፈልጋል።

የጥራት ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ከዚህ ቀደም በርካታ የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውን አስታውሰው የተገኙትን ግብአቶች በማካተት ፖሊሲ እንዲፀድቅ ይደረጋል ብለዋል።

ብሔራዊ የጥራት ፖሊሲው ተግባር ላይ ሲውል አሠራርና አደረጃጀት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና የምርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚቻልበትን አቅጣጫ የሚያስጠብቅ ይሆናልም ነው ያሉት።

በአፍሪካ ደረጃም የጥራት ፖሊሲ መዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያም በአገር ደረጃ ከወዲሁ የጥራት ፖሊሲውን አዘጋጅታ መጠበቋ አስፈላጊ ነው ብለዋለ።

ጥራት ከሌለ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ስለማይቻል ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የምርት ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚገባ በሚኒስቴሩ የጥራት መሠረተ ልማት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር ሳሙኤል ዓለም ተናግረዋል።

ከአፍሪካ ኬንያ፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ሌሎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያወዳደር የጥራት ፖሊሲ እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም