ጃፓን የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ትደግፋለች

80

የካቲት 10/2014/ኢዜአ/ ጃፓን የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ዛሬ የጃፓን ብሔራዊ ቀን መታሰቢያን በኢምባሲያቸው ባከበሩበት ጊዜ ጃፓንና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብትና በሕግ የበላይነት ማስፈን በሚሉት እሴቶች ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው ብለዋል።

በቅርቡም የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በዴሞክራሲና በምጣኔ ኃብት እድገት ጃፓን ያላትን ልምድ ለማጋራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሁ ስኬት በቅርቡ ጃይካ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በጉዳዩ ላይ ሥምምነት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።   

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባትና ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ጃፓን እንደምትደግፍ ነው ያረጋገጡት።  

ጃፓን በተለይም በሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ልምድ ማካበቷን ገልፀው ኢትዮጵያ በመስኩ ለበርካታ ዓመታት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል።

ጃፓንና ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆኑን አንስተው በተለይም በችግር ወቅት እርስ በእርስ የተደጋገፉ አገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ጃፓን ኢትዮጵያ በምጣኔ ኃብትና በፖለቲካው መስክ ለምታከናውነው ተግባር ድጋፎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።

በጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቅጥር ግቢ ዛሬ በተካሄደው የጃፓን ብሔራዊ ቀን መታሰቢያ መርኃ ግብር ላይ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1930 ነበር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የጀመሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም