የሲዳማ ክልል በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

89

የካቲት 10 /2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች 20 ሚሊዮን ብርና  የእንስሳት መኖ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ ለኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አስረክበዋል።

በዚህ ወቅት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ላይ በተከሰተው ድርቅ ህዝቦች ለከፍተኛ ችግር በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ ሲሉ አስረድተው "ድርቁ ያሳደረውን ተጽእኖ ለመቋቋም በአንድነትና በትብብር መስራትና መደጋገፍ ይኖርብናል" ብለዋል።

ለዚህም ነው የሲዳማ ክልል በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ባስከተለው ችግር ለተጎዱ ወገኖች የ20 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የእንስሳት መኖ ድጋፍ ያደረገው ሲሉ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው በህዝቦች ዘንድ መተጋገዝ፣ አብሮ መቆም እና መተባበርን ማጎልበት ከተቻለ ማናቸውንም ችግሮች ተቋቁሞ ማለፍ ይቻላል ብለዋል።

በክልሉ ስምንት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን የገለጹት አቶ ሽመልስ የሲዳማ ክልል ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በክልሉ መንግስት በኩል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ ችግሩን ተቋቁሞ ለማለፍ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመው በክልሉ ትናንሽ የውሃ ግድቦችን በመስራትና ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ጥረት በመደረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ አገራት በዝናብ ወቅቶች የሚጠበቀውን ያህል ዝናብ ባለመጣሉ 26 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ እጥረት እንደተጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያም በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም