ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ በትምህርት፣ በግብርና እና በዲፕሎማሲ መስክ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

69

የካቲት 10/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ በትምህርት፣ በግብርና እና በዲፕሎማሲ መስክ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ።
በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከጉባኤው በተጓዳኝ ከስሎቬኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኔዝ ጃንሳ ጋር ተወያይተዋል።

የመሪዎቹን ውይይት የተከታተሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ፤ መሪዎቹ በውይይታቸው ያነሷቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር አብራርተዋል።

በገለፃቸውም የኢትዮጵያና የስሎቬኒያ ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት እንዲሁም የኢኮኖሚ ትብብሩን ማጎልበት ላይ መምከራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስሎቬኒያ ለኢትዮጵያ ያላትን ድጋፍና አጋርነት በማድነቅ ለስሎቬኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኔዝ ጃንሳ ምስጋና ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

ስሎቬኒያ እኤአ በ2024 የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ለመሆን በዝግጅት ላይ በመሆኗ  ጠቅላይ ሚኒስትር ጃንሳ የኢትዮጵያን ድጋፍ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።

ሁለቱ አገሮች በትምህርት፣ በግብርና ዘርፍ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በቤልጂየም ብራሰልስ በዛሬው እለት የተጀመረው የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ በሁለቱ አህጉሮች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገውን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ ዕድል ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም