ዩኒሴፍ በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

71

ጋምቤላ፤ የካቲት 10/2014(ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት/ ዩኒሴፍ/ በጋምቤላ ክልል ባለፈው ክረምት በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዝብ ድጋፍ አደረገ።

በጋምቤላ ወረዳ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በድርጅቱ የጋምቤላ ክልል ተጠሪ ዶክተር አብዱልሀቅ ዋሂድ እንደገለጹት፤ ዩኒሴፍ ድጋፉን ያደረገው ባለፈው ክረምት በአምስት ወረዳዎች ተከስቶ በነበረው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው  5 ሺህ 800 ወገኖች እንዲውል ነው።

13 ሚሊዮን 192 ሺህ ብር የሆነው ድጋፉ  ለቀጣይ ሶስት ወራት ለምግብ ፍጆታ የሚውል መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ  የጀመረውን ድጋፍ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለእያንዳንዱ ተጎጂ በነፍስ ወከፍ በየወሩ 700 ብር ይሰጣል ብለዋል።

ድርጅቱ የጎርፍ አደጋው በደረሰበት ወቅት የመድኃኒትና የተለያዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፤ ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚዊ የልማት መስኮች ክልሉን ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዛሬ ለተጎጂዎች ላደረገው የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

የጀመረውን የልማት ትብብርና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በክረምቱ ወራት የደረሰው የጎርፍ አደጋ ሰብላቸውንና ንብረታቸው በማውደሙ ለችግር ተዳረገው መቆየታቸውን ተጎጅዎች ተናግረዋል።

ዛሬ የተሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ  የምግብ እጥረት ችግራቸውን ሊቃልላቸው እንደሚችል ጠቁመው፤ ድርጅቱ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በየወሩ ለተጎጂ ወገኖች እንደሚደርስ በሥነ -ሥርዓቱ ላይ  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም