የሲቪክ ማህበራት በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ

54

የካቲት 10/2014 (ኢዜአ)  በአዲስ አበባ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
በከተማዋ የሲቪክ ማህበራት ፎረም ሰብሳቢ ሲስተር አሳየች ይርጋ፤ በሲቪክ ማህበራቱ ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች ከደሞዛቸው በመቀነስ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና አይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ማህበራቱ የሕብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻልና መደገፍ ዋነኛ ስራቸው መሆኑን ጠቁመው ይህ ተግባርም የዚሁ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

በጦርነት ውስጥ ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶችና ህፃናት እንደመሆናቸው በዘላቂነት በመደገፍ ለማቋቋም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የማህበራቱን ድጋፍ የተረከቡት የከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ብርሀኑ ኤኬታ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ማህበራቱ በገቡት ቃል መሰረት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የሲቪክ ማህበራት ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።

ማህበራቱ በጥሬ ገንዘብ 6 ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ብር እና 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

ማህበራቱ ለህብረተሰቡ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ የመንግስትን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም