አሸባሪውን ህወሓት ከሽብርተኝነት የማስወጣት ፍላጎት የሌሎች አካላት እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም

59

የካቲት 10/2014 (ኢዜአ)  አሸባሪውን ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር የማስወጣት ፍላጎት የመንግስት አቋም አይደለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሚኒስቴሩን ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው በኢትዮጵያ ሠላም፣ መግባባትና አንድነት ለመፍጠር አሸባሪው ህወሓት ከሽብርተኝነት መውጣት አለበት የሚሉ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ይህ በአገሪቷ የተከሰተው አለመግባባትና ግጭት በሠላማዊ መንገድ ይፈታል ብለው የሚያስቡ አካላት ፍላጎት እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም አለመሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪውን ህወሓትን ከሽብርተኝነት መዝገብ ለማስወጣት እስካሁን በመንግስት በኩል የተደረገ እንቅስቃሴ የለም ብለዋል።

"እኔም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነኝ" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ አሸባሪው ህወሓትን በተመለከተ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሃሳብ እንደሌለም ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና 'የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል' ስለሚባለው ጎዳይ ከሚመለከታቸው አካላት የተሰጠ ይፋዊ መረጃ እንደሌለም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም