ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የህዝቦችን ትስስር በማጽናት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው

87

ሀዋሳ፤ የካቲት 10/2014 (ኢዜአ) በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር በማጽናት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ- ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ገለጹ።
አፈ ጉባኤው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ አካታች ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት በልዩነት ሲራመዱ የነበሩ  አጀንዳዎች ወደ መድረክ መጥተው የጋራ ድምዳሜ የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

 ይህ ወሳኝ ሀገራዊ መድረክ ስኬታማ እንዲሆን፣ ሂደቱ በአዋጅና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ በህዝብ በተመረጠ ገለልተኛ አካል እንዲመራ ከማድረግ አኳያ በመንግስት በኩል የታየውን ቁርጠኝነትን  አድንቀዋል።

የብዝኀ ማንነት ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታትም  ሆነ ከዛ በፊት በነበሩ ሥርዓቶች በህዝብ ፣ በቡድንና በግለሰቦች ደረጃ የሚነሱ የፍትሕ ፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች  ቢነሱም አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥባቸው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ጥያቄዎቹ የሚነሱበትና የሚስተናገዱበት መንገድ አልመግባባቶችና ግጭቶች እንዲፈጠሩ ብሎም የህዝብ ለህዝብ ትሥሥሮች እንዲላሉ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል።

ብሔራዊ የምክክር መድረኩ በክልሉም ሆነ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲነሱ የቆዩ ሀሳቦች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚስተናገዱበትና የጋራ ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ይህም በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር በማጥበቅ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

መድረኩ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማና መተማመን የሰፈነበት እንዲሆን ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል።

የሚነሱ ሀሳቦች  ያለገደብ የሚስተናገዱበት በመርህ የሚመራ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሲራመዱ በቆዩ የተዛቡ ትርክቶች፣  ከውስጥና ከውጭ በሚፈጠሩ ጫናዎች ሀገርና ህዝብ ችግር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና አፈ-ጉባኤው፤ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለመሻገር የሚነሱ ሀሳቦችና ቅድመ ሁኔታዎች ከሀገር ህልውና አንፃር ሊቃኙ ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ የሚሳተፉ አካላት ገንቢና አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሀሳቦችን በነጻነት በመሰንዘር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

መግባባት የማይቻልባቸው አጀንዳዎች ቢኖሩ  እንኳን በልዩነት ውስጥ መከባበርን በማስፈን እንደ ሀገር እንድንቀጥልና በሂደት እንዲታይ ለማድረግ የሚያስችል መርህን መከተል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም