" ``ኤች አር 6600' ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ያልተገባ ጫና እና በደል ነው"

79

የካቲት 10/2014 (ኢዜአ) 'ኤች አር 6600' ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ያልተገባ ጫና እና በደል መሆኑን አሜሪካዊው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ፡፡

ረቂቅ ደንቡ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ አዲስ ረቂቅ ህግ ያወጣ ሲሆን ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያዝ ነው ተብሏል፡፡

“የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ህግ” በሚል ስያሜ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ፤ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥና አሜሪካን ለኢትዮጵያ የምታደርገው የደህንነትና ፀጥታ ትብብር እንዲቆም የሚደነግግ ነው።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት ሎረንስ ፍሪማን በአሜሪካ ምክር ቤት አባል ማሊኖውስኪ የቀረበው ኤች አር 6600 ረቂቅ ደንብ ለኢትዮጵያ የሚደረጉ የፋይናንስና ሌሎች እገዛዎችን የሚገድብ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፋይናንስ እንዳታገኝ የሚከለክል ስለመሆኑን ጠቁመዋል።፡

በመሆኑም የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ያልተገባ ጫና እና በደል ነው ብለዋል።

ደንቡ በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበርና በታችኛው ምክር ቤት በሚገኙ የዲሞክራት አባላት ተቀባይነት ማግኘቱንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ በማቆም፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ አጠቃላይና ሁሉንም አካታች ብሄራዊ የምክከር ለማድረግ መዘጋጀቱ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ፍሪማን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኤች አር 6600 ረቂቅ ደንብ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን አብራርተዋል።፡

የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን በማዕቀብ ለማዳከም እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያደርገው ጥረት የአሜሪካን ፍላጎት የሚጎዳ በመሆኑ ሊቆም ይገባዋል።

አሁን የሚስተዋለው ጉዳይ አሜሪካና መሰሎቿ የአለም አገራትን በጂኦፖለቲካ ዶግማ የመቆጣጠር ፍላጎት ማሳያ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

 በመሆኑም ፕሬዝዳንት ባይደን ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት የያዙትን የአማካሪዎቻቸውን ሃሳብ ሊቀበሉ አይገባም ነው ያሉት።

 የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ብሎም አጠቃላይ በአፍሪካን በሚመለከት የያዛቸው አቋሞች የተዛቡ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስታቸው ምልከታውን ሊያስተካክል ይገባል ብለዋል።

ኤችአር 6600 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ተጠያቂ ናቸው ያላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርግውን የደህንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም