እያጋጠማቸው ያለው የመብራት መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቸው ተገልጋዮች ጠየቁ

231

ሆሳዕና፤ የካቲት 10/2014 (ኢዜአ)፡ በሆሳዕና ከተማ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ እያጋጠማቸው ያለው የመብራት መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቻው ተገልጋዮች ጠየቁ።
 በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆሳዕና ዲስትሪክት በበከሉ፤ ችግሩን ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በሆሳዕና ከተማ አራዳ ቀበሌ ነጋ ተክሌ የእንጨት ስራ ውጤቶች ማምረቻና መሸጫ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አድነው ነጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤  የመብራት  በተደጋጋሚ ጊዜ  መጥፋት  ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወንም  ሆነ  ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ተቸግረዋል።

''ትዕዛዝ ለሚሰጡን ደንበኞች ትዕዛዛቸውን በጊዜው እንዳናደርስ የመብራት መቆራረጥ መሰናክል ሆኖብናል'' ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤  ይህም ከብዙ ደንበኞቻቸው ጋር እያረራቃቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ገቢያቸው መቀነሱን ጠቅሰው፤  መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ውጭ የእህል ወፍጮ ቤት  ስራ በሌላ  የኃይል አማራጭ ሊሰራ ስለማይችል በስራቸው ላይ መስተጓጎል እንደገጠማቸው የሚናገሩት ደግሞ በከተማዋ የከቡዬ ወፍጮ ቤት ስራ አስኪያጅ  አቶ እሸቱ ሙላቱ ናቸው።

ከከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኙት የነበረው መቆራረጥ ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን ገልጸው፤ ይህም ከፍተኛ  ጉዳት እያስከተለባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

መብራት መቼ እንደሚጠፋና እንደሚበራ ቁርጡ ቢታወቅ እኛንም ሆነ ደንበኞቻችንን  ከመጉላላት ይታደገን ነበር  ብለዋል።

የችግሩ ተደጋጋሚነት በገቢያቸው ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ምግብ ለማብሰልም  ሆነ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ  ቁሳቁሶችን ለመጠቀም መቸገራቸውን የገለጹት  ደግሞ  ወይዘሮ ኃይማኖት ከፍያለው ናቸው።

ይህም በእለት ተእለት ህይወታቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው   ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆሳዕና ዲስትሪክት ዲስትሪቡሽንና ሜንቴናንስ ስራ አስኪያጅ  አቶ ፍሬው ገዛኸኝ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የህብረተሰቡ ቅሬታ ትክክል መሆኑን  አምነዋል።

ችግሩ ሊኪሰት የቻለው  የከተማዋ የኃይል አቅርቦቱና የተጠቃሚ ቁጥር አለመመጣጠን መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የመስመር ለውጥ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሩንም በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ፍሬው፤ ''በዚህ ዓመት በሀገሪቱ የኃይል ማሻሻያ ከሚያደረግባቸው አስር ከተሞች  ሆሳዕና አንዷ መሆኗ የዚሁ ማሳያ ነው'' ብለዋል።

አሁን ላይ የኃይል ማሻሻያ መስመር ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንና የኃይል መቆራረጡ መፍትሔ እንደሚያገኝ  የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ተገልጋዩ  ህብረተሰብ በትዕግስት እንዲጠብቅ ምልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም