ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃን መደራደሪያ ብቻ ሳይሆን የህዝቦች መወያያ መድረክ እንዲሆን በጥንቃቄ መስራት ይገባል

203

አዲስ አበባ የካቲት 10/2014 /ኢዜአ/ ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃን መደራደሪያ ብቻ ሳይሆን የህዝቦች መወያያ መድረክ እንዲሆን በጥንቃቄ መስራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ተናገሩ።
ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ መግባባትን የሚያሰፍን አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን፥ ለኮሚሽኑ አመራሮችን የመመልመል ተግባርም በመከናወን ላይ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፥ እንደ ኢትዮጵያ ጠርዝ ላይ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎችና መጠራጠር የበዛበት ማህበራዊ ግንኙነት ባለበት ሀገር ውስጥ ሀገራዊ ምክክር መደረጉ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በነበራት የፖለቲካ ሂደት ሀገራዊ ምክክርን ቀደም ብላ አካሂዳ ቢሆን ኖሮ አሁን ያገጠሟት ምስቅልቅሎች አያጋጥሟትም ነበር ብለዋል ዶክተር ደሳለኝ።

በመሆኑም አሁን ሊካሄድ የታቀደው ምክክር የጋራ እሴቶችን፣ ሀገራዊ ምልክቶችን ለመቅረፅና የጋራ ታሪክና ፍላጎቶችን ለማንፀባረቅ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

ሀገራዊ ምክክር በሀገራት ታሪክ አንድ ጊዜ ሊካሄድ የሚችል ሁነት መሆኑን ያነሱት የምክር ቤት አባሉ፥ ምክክሩን የፖለቲካ ልሂቃን መደራደሪያ ብቻ ሳይሆን የህዝቦች መወያያ መድረክ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ምክክሩ ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ነጻ ሊሆን እንደሚገባና በየትኛውም ሀገራዊ  ጉዳይ ላይ መነጋገርና መደማመጥ የሚቻልበት መድረክ ሊሆን እንዲገባም ነው ያነሱት።

ምክክሩ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን በጥንቃቄ መሰራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክርን በተገቢው መንገድ ባለማስኬዳቸው የከሸፈባቸው ሀገራት መኖራቸውን በማንሳት  መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ለመድረኩ መሳካት ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ነው የጠየቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም