የፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ለወሎ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

61

ደሴ፤ የካቲት 9/2014 (ኢዜአ ) የፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘበ ድጋፍ አደረገ፡፡
የኢንስትቲትዩቱ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ በድጋፍ ርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ፤ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ  ስራ ለመጀመር  የሁሉንም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይህን የተረዳው ኢንስቲትዩቱ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ዩኒቨርስቲውን መልሶ ለመቋቋም የሚያርገውን ጥረት ለማገዝ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

በተጨማሪም 23 ዓይነት የተለያዩ 448 ነጋሪት ጋዜጣና የህግ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ልማትና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ፤ በአሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት የደረሰበትን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ስራ ለማስጀመር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ ዩኒቨርስቲው  መልሶ እየተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፤ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

መደበኛ ተማሪዎችን በቅርቡ  ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር ዝግጅቱን  እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤የደረሰውን ጉዳት በመረዳት  የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

አሸባሪው ህወሓት በዩኒቨርስቲው ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አፀደ፤ ዩኒቨርስቲው ሙሉ በሙሉ እንዲቋቋም ተቋማት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግልሰቦች  ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም  ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም