ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የኃይማኖት አባቶች ሕዝቡን የማስተባበር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

52

የካቲት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የኃይማኖት አባቶች ሕዝቡ በተረጋጋ መንፈስ እንዲወያይ በማዘጋጀትና በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የኃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ሚና በሚል በአዲስ አበባ ውይይት እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ "ግጭትን በመከላከልና በመቀነስ የኃይማኖት መሪዎች ሚና" እንዲሁም "አገራዊ ምክክር ለሠላምና ለአገራዊ መግባባት" ላይ ፅሁፍ ቀርቧል።

የምክክር የእርቅና ሠላም አማካሪ አቶ ጋረደው አሰፋ ምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የኃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ሕዝቡ ለምክክሩ ዝግጁ እንዲሆን የማስተባበር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የግጭት አፈታትና የሠላም ግንባታ ባለሙያ ቄስ ዶክተር ገለታ ሲሜሶ በበኩላቸው ግጭትን አስቀድሞ በመከላከልና በመፍታት የኃይማኖት መሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ቅራኔዎችን በንግግር ለመፍታት እየተቋቋመ ባለው የምክክር ኮሚሽን ሕዝብ እንዲዘጋጅ የኃይማኖት አባቶች ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

በመድረኩ የተገኙ የኃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በሃይማኖት አስተምህሮ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ፤ የእምነት ተቋማት የጋራ መግባባት በመፍጠር አብሮነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ግጭትን ከመከላከልና ከማስቀረት አኳያም የግጭቶችን አውድ በመረዳትና ለዚያም መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች የታደሙበት ውይይት ነገም ቀጥሎ ይውላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም