ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ ገቡ

129

የካቲት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ ገቡ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብራስልስ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከጉባኤው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚቼል ጋር የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ግንኙነት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ጉባኤው የፊታችን ሐሙስና አርብ የሚካሄድ ሲሆን፤ የሁለቱ ኅብረቶች አባል አገራት መሪዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የሁለቱ አህጉሮች የተለያዩ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ኅብረት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገውን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

በሁለቱ ኅብረቶች መካከል ያለውን የፖለቲካ ግንኙነት በማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድም ጉባኤው ትልቅ ግምት የተሰጠው መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።

መሪዎቹ ብልጽግናን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩ ሲሆን ጎን ለጎንም የአፍሪካ አውሮፓ የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ይፋ ያደርጋል ተብሏል። ፓኬጁ ዓለም ዓቀፍ ችግር የሆኑትን የአየር ንብረት ለውጥና ወቅታዊ የጤና ችግር ከግምት ባስገባ መልኩ ወደ ሥራ እንዲገባ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የ2030 የጋራ ራዕይ ድንጋጌም በጉባኤው የጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዲስ የሰላምና የደኅንነት ማዕቀፍ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥም የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት መሪዎች በጉናኤው ላይ በስፋት ምክክር ያደርጋሉ።

በተጨማሪም ልማትን በፋይናንስ መደገፍ፣ የጤና ሥርዓት ማሻሻልና ክትባት ማምረት፣ ግብርናና ዘላቂ ልማት፣ ትምህርት፣ ባህል፣ የሙያና ሥልጠና ሥርዓትን ማዘመን ላይም መሪዎቹ ውይይት ያደርጋሉ።

ስደትና የሰዎች ዝውውር፣ የምጣኔ ኃብት ትስስር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኃይል ማስተላፍ እና የትራንስፖርት ዘርፎችም የመሪዎቹ የመወያያ አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል።

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት ግንኙነትና የጋራ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 የተጀመረ ሲሆን ጉባኤው በየሦስት ዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል። የመጀመሪያው የኅብረቶቹ ጉባኤ በግብጽ የተካሄደ ሲሆን ፖርቹጋል፣ ሊቢያ፣ ቤልጂየምና ኮትዲቯር በተከታታይ ጉባኤው የተካሄደባቸው አገራት ናቸው።

የዘንድሮ ጉባኤ እ.አ.አ 2020 መካሄድ ሲገባው በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ከተራዘመ በኋላ ነው ነገ በቤልጂም ብራስለስ የሚጀመረው።

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ፣ የጋራ የፓርላማና የኮሚሽን ጉባኤም በመደበኛነት በተለያዩ ጊዜያት ያካሂዳሉ።

ሁለቱ ኅብረቶች የለጋሽና የተቀባይ ግንኙነታቸው ወደ ትብብር እንዲለወጥ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ስትራቴጂ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 አውጥተው አጋርነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም