ከጥጥና ከጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

148

 የካቲት 9/2014(ኢዜአ)አገሪቷ ከጥጥና ከጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ በጥጥና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚስተዋለውን የኃብት ብክነት ለማስቀረትና ተረፈ ምርቶችን በግብዓትነት በመጠቀም የዘርፉን ኢኮኖሚ ማሳደግ ላይ ያለመ ውይይት እያካሄደ ነው።

ውይይቱ 'ሶሊዳሪዳድ' ከተሰኘ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በቡናና በከብት እርባታ ምርቶች ከሚሰራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ጥጥ በስፋት የማምረት አቅም ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች።

ይሁንና የምርት ሂደቱ በሚፈለገው መልኩና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለመታገዙ አገሪቷ ካላት የጥጥና የጨርቃ ጨርቅ ምርት አኳያ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ዘርፉን የሚያሳድጉ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባሻገር የሥራ ዕድልም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከቀጥተኛ ምርት በተጨማሪ ተረፈ ምርቶችን መልሶ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም እንዲሁ።

ለዚህም ኢንስቲትዩቱ አምራቾችን በማሳተፍ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

በምርት ሂደትና በአቅርቦት ዙሪያ አምራቾች ለሚያነሷቸው የአሰራር ክፍተቶች ምላሽ ለመስጠት በቅርበት መነጋገር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሌሎች አገራትን ተሞክሮ እንደ መነሻ በመውሰድ በቀጣይ የተሳካ ሥራ ለመሥራት ኢንስቲትዩቱ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሰፕላይ ኢኮኖሚ ኔትወርክ የኢትዮጵያ ወኪል ወይዘሮ ቤዛዊት እሸቱ ተረፈ ምርቶችን መልሶ መጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምርቶች የሚስተዋል አሰራር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚ እድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የገቢ ማግኛ ዘዴ እንደሆነም አንስተዋል።

ምርት አምርቶ ከመጠቀም ባለፈ ተረፈ ምርቶችን መልሶ መጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ተጨማሪ ገቢ ለማመንጨት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም በጥጥና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ምርቱንም ሆነ ተረፈ ምርቱን በአግባቡ መጠቀም ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም አምራች ሃይሉን ማብቃት፣ ሙያዊ ሥልጠናዎችን ማመቻቸትና የገበያ ትስስር መፍጠርን ዋነኛ ተግባር ሆኖ ሊወሰድ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በኢንስቲትዩቱ የጥጥ ልማት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አሰፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጥጥ ምርት አመቺ መልክዓምድራዊ ሁኔታ ያላት ቢሆንም የገቢ ምንጭነቱ ላይ በበቂ ባለመሰራቱ የምርት ምጣኔው አነስተኛ ነው ብለዋል።

ባደጉ አገራት ዘንድ የጥጥ ፍላጎት እየጨመረ ቢሆንም በዚያው ልክ ትኩረት እንዳልተሰጠው ገልጸዋል።

ፍላጎቱን እንደ ዕድል በመጠቀም የአገሪቷን የምርታማነት አቅም መጠቀምና አምራቾችን ወደ ዘርፉ መሳብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስረጽና የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራትን ተሞክሮ መቅስም እንደሚገባም አክለዋል።

በጥጥ ምርት የተሰማሩ አምራቾችም ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ በቂ የገበያ ትስስር አለመፈጠር፣ ግብዓቶችን በጥራትና በብዛት አለማግኘት፣ አጋዥ ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት አለመሟላት ካነሷቸው ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ቢሾፍቱ ላይ እየተካሄደ ያለው ውይይቱ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም