በቻግኒ ከተማ ለህገ ወጥ ሽያጭ የተዘጋጁ የጦር መሳሪያዎች ከተጠርጣሪዎች ጋር ተያዙ

125

እንጅባራ ፤ የካቲት 9/2014(ኢዜአ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ለህገ ወጥ ሽያጭ የተዘጋጁ የጦር መሳሪያዎችን ከተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር መያዙን ፖሊስ አሰታወቀ።
የጦር መሳሪያዎቹ ከነተጠርጣሪዎቹ ጋር  የታያዙት በከተማው ቀበሌ  04 ልዩ ስሙ "ቦሌ ሠፈር" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት መሆኑን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተወካይ ምክትል ኮማንደር አድገህ ልመንህ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከህብረተሰቡ የደረሰ ጥቆማን መሰረት በማድረግ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ  መቆጣጠር እንደተቻለ አስረድተዋል።

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል አራት  ክላሽንኮቭና  አንድ ባለ ሳንጃ ኤስ.ኬ.ኤስ ጠብ መንጃዎች ፣ 818 የክላሽንኮቭ ጥይትና የተለያዩ  የጦር መሳሪያዎች   አካላት ይገኙበታል።

ምክትል ኮማንደር አድገህ እንዳሉት፤ በህገ ወጥ ድርጊቱ የተጠረጠሩ  ባል እና ሚስት  በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው፤ የጦር  መሳሪያዎቹ ለህገ ወጥ ሽያጭ  ለማዋል የተዘጋጁ እንደነበር ተናግረዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የህዝብና የአካባቢን ሰላም ከማሳጠት ባለፈ የወንጀል ድርጊቶች እንዲስፋፉ ካለው የጎላ አስተዋጽኦ አንፃር ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያይ ፈጥኖ በመጠቆም ትብብሩን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም