የኢሉባቦር ዞን በድርቅ ለተጎዱ የፈንታሌ ወረዳ ወገኖች የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ ላከ

58

መቱ ፤የካቲት 9/2014 (ኢዜአ) ከኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች የተሰበሰበ የምግብ አህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ተላከ።
ወደ ስፍራው የተላከው 3 ሚሊዮን 180 ሺ ብር ግምት ያለው የምግብ እህልና የእንስሳት  መኖ  መሆኑን የዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ አበራ ገልጸዋል።

በዚህ  ሁለተኛው ዙር ከዞኑ ነዋሪዎች  የተሰበሰበው ድጋፍ 1ሺህ 60 ኩንታል የምግብ እህል እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚሆን በሦስት ተሽከርካሪዎች የተጫነ ሳር መሆኑ ተመልክቷል።

ድጋፉ ወደ ስፍራው በተላከበት ወቅት የተገኙት የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ፤ በዜጎቻችን ላይ በሚደርሰው ችግር የሚረዳንን አካል ከውጭ ከመጠበቅ እኛው እርስ በርሳችን  በመረዳዳት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስም የዞኑን ማሕበረሰብ በማስተባበር ድጋፍ የማሰባሰብ ስራው  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በምቹ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ማህበረሰብ በድርቅ የተጎዱ አከባቢዎችን በሚያስፈልጋቸው ለመደጋገፍ ብዙ ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ  የመቱ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገረሙ ብርሃኑ ናቸው።

የቆየ የኢትዮጵያዊ መረዳዳት ባህላችን ወገኖቻችንን በመደገፍ በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ በበኩላቸው፤ በሚያጋጥሙን መሰል ችግሮች ከእኛ ውጭ ለወገኖቻችን ቀድሞ እንዲደርስ የሚጠበቅ ሌላ አካል እንደሌለ በማሰብ ለወገን ደራሽነታችንን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

"ለወገን ደራሽ ወገን ነው" በሚል ተነሳሽነት የዞኑ ነዋሪዎች በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 3 ሚሊዮን 450 ሺህ  ብር ግምት ያለው የምግብ እህልና አራት ተሽከርካሪ የእንስሳት መኖ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም