በደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተባለ

84
ሃዋሳ ነሃሴ 26/2010 ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ በመጭው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለፀ። የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት በክልሉና አጎራባች ዞኖች  ተከስተው በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እየተከናወነ ነው። የክልሉ መንግስትና መሪው ድርጅት ደኢህዴን ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ከሀምሌ 2010 አጋማሽ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ። "ዜጎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ጎን ለጎን ሰብአዊና ቁሳዊ ድጋፍ የማቅረብ፣ ለግጭት ምክንያት የሆኑ አካላትን ተጠያቂ የማድረግና ተመሳሳይ ክስተት እንዳይደገም የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው " ብለዋል ። በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃዮች ከሚገኙበት  ጌዲኦ ዞን እሰካሁን 319ሺህ 61 ዜጎች ወደ ቀያቸው  መመለሳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። ሃዋሳ ላይ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ከ3ሺህ 250 በላይ አባወራዎችም በመልሶ ማቋቋምና ድጋፍ ፓኬጁ የሶስት ወር ቤት ኪራይና የአንድ ወር ቀለብ ተሰጥቶዋቸው ወደ ቀድሞ ህይወታቸው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል ። ለአንድ ዓመት ያህል በመጠለያ ጣቢያ የቆዩ 40 ሺህ የሚደርሱ የአማሮና ቡርጂ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የፌደራልና የክልል አመራሮች ከህዝቡ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን አውስተዋል ። በግጭት ምክንያት ተዘግተው የቆዩ ከአማሮ ፍስሃ ገነትና ከቡርጂ ወደ ሃገረ ማርያም የሚወስዱ መንገዶች ተከፍተው የህዝብ ለህዝብ ግንኙት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ "ተፈናቃዮቹ ከግብርና ስራቸው ለወራት ርቀው የቆዩ በመሆናቸው ፈጥነው ወደ እርሻ ስራ እንዲገቡ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፉ ይጠናከራል" ብለዋል፡፡ ለተፈናቃዮች ለስድስት ወራት የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚቀርብና በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በፌደራል መንግስት አማካኝነት የመኖሪያ ቤት ግንባታና ጥገና ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል ። በክልሉ ካፋ፣ ሸካ፣ ዳውሮ፣ ጋሞጎፋና ኮንታ ልዩ ወረዳዎችም ባጋጠሙ ግጭቶች ለተጎዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፎች እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን ከዚሁ ጎን ለጎን ሰላምን የማስጠበቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "በተከሰቱ ግጭቶች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል" ያሉት አቶ ጥላሁን በወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤ፣ለኩና ይርጋለም ከተሞች የንግድ ቤቶችና የመንግስት ተቋማት መውደማቸው ለአብነት ጠቅሰዋል ። "በአካባቢዎቹ የወደሙ ንብረቶችን የማጥናት ሰራ የተጠናቀቀ በመሆኑ የክፍያ ስርዓት ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል " ብለዋል ። እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ በክልሉ በግጭት የደረሱ ውደመቶችን ለመተካት ኮሚቴ ተቋቁሞ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም