የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በጥምረት መጠቀም ያስፈልጋል

155

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 09/2014(ኢዜአ) የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በጥምረት መጠቀም እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራንና ተመራማሪዎች አስገነዘቡ።

በኢትዮጵያ የአፈር መከላት የአፈር እርጥበት እንዳይኖርና ለም አፈር ተጠርጎ እንዲወሰድ በማድረግ ከፍተኛ ችግር መሆኑ ይነገራል።

የአፈር ለምነት አለመኖር ደግሞ ለግብርና ምርት መቀነስ አይነተኛ ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎችና ምሁራን ይናገራሉ።

በደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ተቋም ተመራማሪ ሙሉጌታ ማርቆስ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተው የአፈር ለምነት መታጠብ ለምርት መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የአፈር መታጠብን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው የአፈር እርጥበትን ለማቆየትና ለምነቱን ለማስጠበቅ ሌሎች አማራጮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በጥምረት በመጠቀም አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ይመክራሉ።

እንደ ተመራማሪው ገለፃ የሰው ሰራሽ ና ተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) በጥምረት  በመጠቀም ውሀ የማስረግና እርጥበት የመያዝ አቅምን በማጎልበት የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ምርትን ማሻሻል ይቻላል፡፡

በፋብሪካ የሚመረቱ ማዳበሪያዎች ብዙ ጊዜ በአፈር ውስጥ ስለማይቆዩ ከአንድ የምርት ወቅት በላይ የማያገለግሉ መሆኑ በዘላቂነት የአፈር ለምነትን እንደማያስጠብቁም ያስረዳሉ።

በመሆኑም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን አጣምሮ በመጠቀም እርጥበትና የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ምርታማነትንም መጨመር ይቻላል ሲሉ ይመክራሉ።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የእፀዋት ሳይንስ መምህሩ ችግኜ አዳሙ፤ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በጥምረት መጠቀም የመሬት ለምነትን ከመጠበቅና ምርትን ከመጨመር ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ያስረዳሉ።

የፋብሪካ ማዳበሪያ በውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ ወደ አገር ወስጥ የሚገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አቅርቦቱ አስተማማኝ ዋጋውም ተመጣጣኝ የማይሆንበት አጋጣሚ ስለመኖሩም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማደበሪያን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር በጥምር መጠቀም ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን በግለሰብ ደረጃ ከማከናወን ጀምሮ የአፈር ለምነት የሚጨምሩ ሰብሎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ደጋ አካባቢ ዝናብ የሚበዛበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአፈር ለምነት ተሟጦ የአሲድነት መጠኑ አድጎ እስከ 41 በመቶ በአማካኝ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በርካታ እፅዋቶች ለማደግ ከአስራ ሰባት ያላነሱ ንጥረ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የጠቀሱት መምህሩ የአሲድነት መጠንን መቀነስ፣  የአፈሩን ለምነትና እርጥበት መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም