በጋምቤላ ክልል ከ268 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚካሄድ የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

69

ጋምቤላ፤ የካቲት 8/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ከ268 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ገንዘብ የእናቶች፣ የህፃናትና ሌሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆነ።

‘‘ለስርዓተ-ፆታ እኩልነት በማህበራዊ ጤና ቁርጠኝነት’’ በሚል መረሃ ግብር በክልሉ አራት ወረዳዎች በሚተገበረው ፕሮጀክት  ከ125 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ሥነ-ሥርዓት ላይ  እንዳሉት፤  ፕሮጀክቱ በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለእናቶችና ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ረገድ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሻሉ ስራዎች ቢከናወኑም ለእናቶችና ህፃናት ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ከማቅረብ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የእናቶችንና ህፃናትን ህመምና ሞት ለመቀነስና ስርዓተ ምግብን በማሻሻል ጤናማና አዕምሮው የዳበረ ዜጋ ለመፍጠር ዛሬ  ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት በክልሉ የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሩት ጋትዊች በበኩላቸው፤ በክልሉ የጤና አገልግሎት ሽፋን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ቢታይም በጥራት በኩል ብዙ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት የለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በክልሉ ጤና ቢሮ " የስርዓተ ፆታ እኩልነት በማህበራዊ ጤና ቁርጠኝነት " ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ኡጁሉ ኡጁሉ፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት በእናቶችና ህፃናት ጤናና በስርዓተ ምግብ ማሻሻያ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአራት ወረዳዎች በሚኖረው የሶስት ዓመት ቆይታ ከ125 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤  ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአውሮፓ ህብረት ከ268 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ድጋፍ መገኘቱን አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም