የሴቶች ኮከስ ፎረም ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል

95
አሶሳ ነሀሴ 26/2010 በየደረጃው የሚገኙ የሴቶች ኮከስ አባላት  ከአገራዊ ለውጡ እኩል አቅማቸውን በማጠናከር ለሴቶች ተጠቃሚነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ ሀገራዊ የሴቶች ኮከስ ፎረም ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የፎረሙ ተወካይ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኮከሱ በየደረጃው የሚገኙ የተለያዩ አደረጃቶችን በመጠቀም ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቦአል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ክልሎች አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳልቆሙ ተናግረዋል፡፡ የችግሮቹ ምክንያትም የኮከሱ አባላት ለሴቶች ተጠቃሚነት በሙሉ አቅማቸው አለመንቀሳቀሳቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ “ኮከሱ ሴቶችን የሚያጠናክሩ በርካታ ሥራዎችን ይጀመራል እንጂ አይጨርስም” ያሉት ተወካይዋ ምክንያቱ ደግሞ “ቁርጠኛ ሆነው አለመሠራታቸው ነው” ብለዋል፡፡ ኮከሱ በአዋጅና ደንብ የታገዘ መሆኑን ገልጸው ይህንን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡ ''የኮከሱ አባላት ራሳችንን በተሻለ እውቀት በማነጽና ግንዛቤአችንን በማስፋት አሁን ያለውን አገራዊ ለውጥ በሚመጥን መልክ ለሴቶች ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ይገባናል'' ብለዋል፡፡ የኮከሱ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ እምዬ ቢተው ኮከሱ በ2011 የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚጨምሩ ዘጠኝ ዋነኛ ግቦችን እንዳስቀመጠ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴቶችን አመራርነት ድርሻ ወደ 50 በመቶ ማሳደግ የእቅዱ አንዱና ዋኛው ትኩረት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ድርጊቶችን በጥናት በመለየት መፍትሄ ለማስቀምጥ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡ ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም የፎረሙ አባላት ተቀናጅተው ባለመስራታቸው የተከሰቱ ችግሮችን ከነመፍትሄው ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ፈቲሀ መሀመድ በበኩላቸው አስፈጻሚው አካል በሥራ እድል ፈጠራ ወቅት እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ የሥራ ፈላጊ ሴቶችን ቁጥርና ተያያዥ ጉዳዮች ያማከለ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዳይሻሻልና ራሳቸውን እንዳይችሉ ማድረጉን ጠቅሰው ''በየደረጃው የምንገኝ የኮኮሱ አባላት ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀራርበን ችግሩን መታገል አለብን'' ብለዋል፡፡ በፎረሙ ላይ የሁሉም ክልል  ምክር ቤቶች ሴት አፈ-ጉባኤዎች የተሳተፉ ሲሆን የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግስት መስሪያ ቤቶች የህጻናት ማቆያዎችን ለመክፈት ያደረጉት ጥረት እንደመልካም ተሞክሮ ተወስዷል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም