ፖሊስ የአሸባሪው ሸኔ አባላትን ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር አዋለ

74

ጭሮ፣ የካቲት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሚኢሶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎችን ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ አዛዥ ዋና ሳጂን አህመዲን ከድር ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፖሊስ 12 የሽብር ቡድኑን አባላት በቁጥጥር ስር ያዋለው ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ ዳለቻ ቀበሌ ልዩ ስሙ በሬዳ በተባለ ስፍራ ነው።

የሽብር ቡድኑ አባላት በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ስምንቱ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቆስለው በቁጥጥር ስር ሲውሉ፤ አራቱ ግን ለፖሊስ በሰላም እጃቸውን ሰጥተው ነው ብለዋል።

ዋና ሳጂን አህመዲን የአሸባሪ ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ታጥቀዋቸው የነበሩ ጠመንጃዎች፣ ከሁለት ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች፣ የተለያዩ አልባሳትና በጭሮ ወረዳ ስም የተቀረጹ ሀሰተኛ ማህሞች ተይዘዋል።

ከዚህም ባሻገር ለሽብር ቡድኑ መረጃ በማቀበል ተባባሪ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦችም በህግ ጥላ ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን አዛዡ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅና ፀጉረ ልውጦች ሲያጋጥሙት ጥቆማ በመስጠት ከፖሊስና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም