ፍርድ ቤቱ ሰው በማገት ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በ22 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ

73

መተማ፣  የካቲት 8/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ሰው አግተው ከቤተሰቦቻቸው 160ሺህ ብር የተቀበሉ ሁለት ግለሰቦች እያንዳንዳቸውን በ22 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ትናንት መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ አበበ ማስሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ በዋና ተከሳሽ አምሳሉ አዱኛ እና በግብረ አበሩ ካበው አዳነ ላይ የእስር ቅጣቱን የወሰነው ጥፋተኝነታቸውን በማስረጃ በማረጋገጡ ነው።

ግለሰቦቹ በዞኑ መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ህዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ማሽላ ወቅተው አውድማ ላይ ምርት ይጠብቁ የነበሩ ሁለት ሰዎችን በጦር መሳሪያ አስፈራርተው ከምሽቱ 4 ሰዓት አግተው ወስደዋል ብለዋል።

እንደ አቶ አበበ ገለጻ ግለሰቦቹ ሰዎቹን ካገቱ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው 160ሺህ ብር ተቀብለው መልቀቃቸውን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ አረጋግጧል።

ግለሰቦቹ ከአገቷቸው ሰዎች ቤተሰቦች ገንዘቡን የተቀበሉት ዋና ተከሳሽ አምሳሉ አዱኛ እና ካበው አዳነ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የጦር መሳሪያ በመያዝ  መሆኑንም አመልክተዋል።

የግለሰቦችን ጥፋተኝነት በዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ትናንት ባስቻለው የወንጀል ችሎት እያንዳንዳቸውን በ22 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል ብለዋል።

የሰው እገታ  ወንጀሉን ሰባት ሆነው የፈጸሙት ሲሆን፤ ከመካከላቸው ሶስቱ  ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ባስቻለው ችሎት እያንዳንዳቸው  በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስረድተዋል።

አቶ አበበ እንዳሉት እስካሁን ያልቀረቡ ሌሎች ሁለት የወንጀሉ ተጠርጣሪ ተባባሪዎችን ፖሊስ አፈላልጎ ለህግ እንዲያቀርብ  ፍርድ ቤቱ  ትዕዛዝ  ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም