በመዲናዋ በታሪካዊ ቅርስነት ለተመዘገቡ 138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በታሪካዊ ቅርስነት ለተመዘገቡ 138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ተሰጠ
60
አዲስ አበባ፣ የካቲት 08/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በመዲናዋ በታሪካዊ ቅርስነት ለተመዘገቡ ለ138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ሰጠ።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በመዲናዋ የሚገኙ ቅርሶችን ለመለየት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።
በዚህም በዛሬው እለት በመዲናዋ በታሪካዊ ቅርስነት ለተመዘገቡ 138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የእውቅና ምስክር ወረቀቱ የቅርስ ባለይዞታዎች ቅርሱን ተንከባክበው ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በቢሮው የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ስዩም፤ በ2013 በተካሄደው የቅርስ መመዝገብና የመከለስ ሥራ 316 ቅርሶች መለየታቸውን አስታውሰዋል።
ከተለያዩ ቅርሶች መካከል ለ138ቱ የእውቅና ሰርተፍኬት መሰጠቱን ገልጸው በቀጣይ ደግሞ ለቀሪዎቹ የምስክር ወረቀት ይሰጣል ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።